ሰው ምንድርን ነው?

ሰው ምንድርን ነው? 

‘ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል’ ወደሚለው ስሕተት እና ሐሳውያኑ ስለሚያቀርቧቸው አሳሳች አጠቃቀሶች ከመግባቴና ስሕተቱን ከመግለጤ በፊት ግን በቅድሚያ ትክክለኛውን፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት በአጭሩ  እንመልከት። ይህንን የምጀምርበትን ትምህርት መደምደሚያውም አደርገዋለሁ። 

ሰው ምንድርን ነው? በአጭሩ፥ ሰው ሰው ነው። ሰው ሲፈጠር ሰው፥ ሲኖር ሰው፥  ሲሞት ሰው፥ ከሞት በኋላም እንኳ፥ በትንሣኤም ሰው ሰው ነው። ካላወቅን እንወቅ፤  ሰው ሰው ነው። ሰው ከሌሎች አካላውያን ፍጡራን ሁሉ የላቀና የፍጡራኑ ሁሉ ቁንጮ የሆነ ፍጡር ነው። የፈጣሪያችን የእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ መሆናችን  ብቻውን እንዴት የከበረ ነገር ነው! ያ ሰው ሆነን በመልኩ እንደ ምሳሌው መፈጠራችን ልካችን ነው፤ ያልበዛ፥ ያልተንዛዛ፥ ያላነሰ፥ ያልጎደለ ልካችን። ሰው  መሆን በልካችን የተሠራ ማንነታችን ነው። ሰው ሲፈጠር ሰው ነው፤ በምድር  ሲመላለስም ሰው ነው። ከውድቀት በፊት ሰው፥ ከውድቀት በኋላም የእግዚአብሔር  መልክና ምሳሌ የሆነ ሰው ነው፤ ዘፍ. 1፥26-27፤ 2፥7፤ 9፥6። ከውድቀት በኋላም፥  ማለትም ከዘፍ. 3 በኋላም የሰውን ሰውነት ኃጢአት በከለውና ከአምላኩ ለየው እንጂ ሥሪቱ አልተቀየረም። የሰው ሰውነት ወይም ማንነት ዘላለማዊ ነው። ሰው ለዘመን  ብቻ ሳይሆን ለዘላለምም ሰው ነው። 

ሰው መንፈስ ነው የሚሉ ሰዎች ከጅምሩ የተሳሳቱ መሆናቸውን የጅምሩ መጽሐፍ  ያረጋግጥልናል። ሰው በውስጡ መንፈስ አለ እንጂ መንፈስ አይደለም። ሰው መንፈስ  ቢሆን ኖሮ፥ ገና ሲፈጠር እግዚአብሔር፥ መንፈስን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን  እንፍጠር ይል ነበር። ቃሉ ግን፥ በዘፍ. 1፥26፤ እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን  [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር  ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። ይላል። ‘እንፍጠር’ ያለው መንፈስን ሳይሆን ሰውን  ነው። ቁጥር 27 ደግሞ፥ እግዚአብሔርም ሰውን [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። 

ይላል። በመልኩ የፈጠረው ሰውን እንጂ መንፈስን አይደለም። ወንድም ሴትም  በመልኩ የተፈጠሩ ሰዎች ናቸው። ሰዎች ሰዎች ናቸው፤ መናፍስት ወይም መንፈሶች  አይደሉም። 

በዘፍ. 2፥7 እግዚአብሔር አምላክም ሰውን [መንፈስን አይደለም፤ ሰውን] ከምድር  አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም [መንፈስ  አይደለም፤ ሰው] ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ይላል። ይህ እዚህ ዘፍ. 2፥7 ላይ የተብራራው ያ እዚያ ዘፍ. 1፥26-27 የተፈጠረው ነው። ሰው እዚያ በስድስት ቀናት ሁሉ ነገር ሲፈጠር የተፈጠረበትን፥ የተሠራበትን፥ የተበጀበትን መንገድ መናገሩ እንጂ  ሌላ ታሪክ አይደለም። አንዳንድ አሳቾች ይህንን የሰው አፈጣጠር ምንባብ እንደ ሌላ ፍጥረት፥ እንደ ሌላ ሥሪት አድርገው፥ ወይም ከተፈጠረ በኋላ ሌላ ተጨማሪ ንጥረ  ነገር እንደተገጠመለት አድርገው ሊያቀርቡ ይሞክራሉ። ዘፍ. 2፥7 የዘፍ፣ 1፥26-27 

ከሳችና ማብራሪያ ብቻ ነው። እዚያ ሰው ተፈጠረ፤ እዚህ ደግሞ እስትንፋስ እፍ  ስለተባለበት ሕያው ነፍስ ሆነ ይላሉ። ስሕተት ነው። ከሆነም ደግሞ፥ ሰው ነፍስ ነው   ማለት ነው የነበረባቸው እንጂ፥ መንፈስ ነው ማለት አልነበረባቸውም። አሳቾቹ ነፍስ አለው ከማለት ይልቅ ‘ሰው ነፍስ ነው’ ቢሉ ነበር የሚቀርበው። ምክንያቱም፥ ሰውም   ነፍስ ያለው ሆነ። ስለሚል። መንፈስ ሩኻ ወይም ሩዋኽ ነው የሚባለው  በዕብራይስጥ። ዘፍ. 1፥2 ላይ ያለው የእግዚአብሔር መንፈስ የሚለው ሩኻ ኤሎሂይም ወይም ሩዋኽ ኤሎሂይም ነው። በአማርኛም ሩህ እንላለን። ከዚያ  የመጣ ነው። ሕያው ነፍስ ሆነ የሚለው ግን ኻያህ ኔፌሽ  ׁ ነው። በዕብራይስጥ ኔፌሽ በአማርኛ ነፍስ ነው። ይህም ከዚያ የመነጨ ነው። ስለዚህ ሰው 
መንፈስ አይደለም። ነፍስም አይደለም፤ ሰው ሰው ነው እንጂ። 

ከዚህ ክፍል የምንረዳው ሰው ወይም የሰው አፈጣጠር በመጀመሪያ መንፈስ ተፈጥሮ ያ መንፈስ ሥጋ ሲመረግበት አይደለም። ሰው ከአፈር ተፈጥሮ ከዚያ ከእግዚአብሔር  የሕይወት እስትንፋስ እፍ ሲባልበትና ሕያው ነፍስ ያለው ሲሆን ነው። ልብ እንበል፤ ነፍስም አልተባለም፤ ‘ሕያው ነፍስ ያለው’ ሆነ። ሕያው ነፍስ ያለው ምን? ሕያው  ነፍስ ያለው ሰው። የተፈጠረው ሰው ነዋ! ሕያው ነፍስ ያለው መንፈስ አልተባለም።  ሰውን በተመለከተ፥ ‘መንፈስ’ የሚለው ቃል በዚህ ሰው በተፈጠረበት ታሪክ ውስጥ  ጨርሶም የለም። ስለዚህ የመጀመሪያው ሰው አዳም፥ ምንድርን ነው? ሰው ነው። 

የመጀመሪያዋ ከአዳም አጥንት የተሠራችው ሴትም ምንድርን ናት? ሰው ናት፤ ሴት  ሰው፤ በጾታ ሴት የሆነች ሰው።  

የማስተምረው ስለ ሰው ሰው-ነት፥ ወይም ሰው ሰው ስለመሆኑ ነው። ከላይ ስለ ሞኝ  ጥያቄ እንዳልኩት አንዳንድ ጊዜ፥ መነገር እስከማይገብባቸው ድረስ ግልጽ የሆኑ  ነገሮችን እንድንናገር የሚያደርጉት ግልጹን የሚሰውሩ ሰዎች ናቸው። ሰው ሰው  መሆኑ በጣም ግልጽ የሆነ እውነት ሆኖ ሳለ ሰውን ሰው አይደለም፤ ሰው መንፈስ ነው የሚሉ አሳቾች ቀድሞም ግልጽ የሆነውን ነገር እንደገና እንድንናገረው ያደርጉናል። 

እነዚህ ሰዎች ሰው ሰው መሆኑ ግልጽ ሆኖ ሳለ፥ ‘ሰው መንፈስ ነው እንጂ’ በማለት ጥቅስ እየገመዱና እያጠናገሩ ሰውን ያደናግራሉ፤ ያደናቁራሉ። ‘ሰው መንፈስ ነው’  ሲሉ፥ ሰው ሰው አይደለም ማለታቸው ነው። 


ሰውን መንፈስ የሚያሰኙት ሰዎች ከአፈጣጠሩ የሚወስዱት አሳብ በመልኩና  በምሳሌው መፈጠሩን ነው። ያም፥ ‘እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ሰው በመልኩና  በምሳሌው ከተፈጠረ ሰውም መንፈስ መሆን አለበት’ ነው። መነሻቸውና  ድምዳሜያቸው ወይም መድረሻቸው ይህ ነው። ግን በግልጽ ከተጻፈው እውነት ነው የምንንደረደረውና፥ እግዚአብሔር ሰውን ነው በመልካችንና በምሳሌያችን እንፍጠር  ያለው እንጂ መንፈስን አይደለም። ስለዚህ ያ የተፈጠረው ነገር፥ ማለትም ሰው፥  የፈጣሪው ምሳሌና መልክ አለው ማለት ነው እንጂ ትንሽ እግዜር አልተፈጠረም። 
ሰው ነው የተፈጠረው።  

መልክና ምሳሌው መንፈስነቱ ከሆነ ደግሞ፥ የተፈጠረው ሰው አካል ስላለው፥ ሥጋ  ስላለው፥ ቁስ ስለሆነ፥ እንዲህም ሆኖ አምሳል ስለሆነ፥ የአምሳሉ፥ የመልክና ምሳሌው  ምንጭ የሆነው እግዚአብሔርም አካልና ቁስ ነው ማለት ነው፤ ወይም አካልና ቁስ  ሊሆን ነው ማለት ነው። ነገር ግን እግዚአብሔርም አካል አይደለም፤ ቁስም አይደለም። ስለዚህ የሰው መልክና ምሳሌነት፥ መንፈስነት ሳይሆን ሰው ሳለ አምላኩን መምሰሉ ነው። 

እንዴት ነው የሚመስለው? በብዙ ዘርፎች ነው ሰው ፈጣሪውን የሚመስለው። ገዢ  መሆኑ፥ እውቀትን የሚያውቅ መሆኑ፥ መንፈስ ስላለውና፥ ከአምላኩ ጋር ግንኙነት  ስለሚያደርግ፥ ወዘተ። ሰው ሲፈጠር መንፈስ ሳይሆን መንፈስ ያለው ወይም  መንፈሳዊ ፍጡር ነው። ሰው ሲፈጠር በሥጋ ውስጥ የሚያድር መንፈስ ሳይሆን፥  በሥጋው ውስጥ፥ በሰውነቱ ውስጥ፥ በውስጡ ሕያው ነፍስም መንፈስም ያለው ሰው  የተሰኘ፥ ሰው የተባለ፥ ሰው የሆነ ፍጡር ነው። ከሌሎች አካል ካላቸው ፍጥረታት  ሁሉ የተለየና ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት፥ ግንኙነት ማድረግ የሚችል፥ ማምለክ፥ 
ለእግዚአብሔር ምላሽ መስጠት የሚችል ፍጥረት ሰው ብቻ ነው። አካል ካላቸው  ፍጥረታት ሁሉ ያልኩት መላእክትን ከስሌቱ ውስጥ ለማውጣት ነው። መላእክት  መናፍስት ወይም አካል የለሽ ፍጡራን ናቸው።

 መንፈስ ማለት በፍጥረቱም፥  በትርጉሙም ረቂቅ፥ አካል አልባ፥ ቁስ ወይም ቁሳዊ ያልሆነ ማለት ነው። መንፈስ  ቁሳዊ አይደለም፤ ቁስም የለውም። ሰው መንፈስ ነው ሲባል የዚህ ትርጉም ተቃራኒ  ነው። ሰው መንፈስ ነው ማለት ቁስ የለውም፥ አካል የለውም ማለት ነው። ይህ በራሱ ተቃርኖ ነው። ትምህርቱን ስሑት የሚያደርገው አንድ ነጥብም ይህ ነው። 

ከላይ እንዳየነው፥ እግዚአብሔር በመጀመሪያ መንፈስን አልፈጠረም፤ አዳም መንፈስ  አልነበረም። ሔዋንስ? ሔዋንም ከሥጋ የተገኘች ሥጋ እንጂ መንፈስ አልነበረችም።  የሔዋንንም አፈጣጠር እንመልከት፤ ዘፍ. 2፥23፤ አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት  ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ነው  የተባለው። በቀዳሚ ጽሑፉ፥ ‘ከኢሽ ተገኝታለችና ኢሻ ትባል’ ነው የሚለው። 


ደግሞም፥ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ ናት፤ ነው ያለው እንጂ፥  ‘ይህች መንፈስ ከመንፈሴ ናት’ አላለም። እግዚአብሔር በመጀመሪያ መናፍስትን  አልፈጠረም። ሰዎችን ነው የፈጠረው። አጥንት ከአጥንቴ፥ ሥጋም ከሥጋዬ። 

ሰው ሥጋና አጥንት አለው። አዳም ሥጋና አጥንት ካለው፥ ሔዋን ሥጋና አጥንት  ካላት አዳምና ሔዋን ሰዎች ናቸው እንጂ መንፈሶች አይደሉም። መንፈስ ሥጋና  አጥንት የለውም። መንፈስ ሥጋና አጥንት እንደሌለው የነገረን ጌታ ኢየሱስ ራሱ ነው። ከትንሣኤው በኋላ በዚያው በተነሣበት ቀን ወደ ኤማሁስ ይሄዱ ከነበሩት ከነቀለዮጳ  ጋር ከሄደ፥ ወደ ቤታቸው ከገባ በኋላ፥ እራት አብረው ሲበሉ፥ እንጀራ ቆርሶ ሲሰጣቸው፥ ዓይናቸውም ተከፈተ፥ አወቁትም፤ እርሱም ከእነርሱ ተሰወረ። (ሉቃ.24፥31)። 

እነዚህ ሰዎችም በዚያች ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ ሲመለሱም አሥራ አንዱና ሌሎችም ከነሱ ጋር ተሰብስበው ስለ መነሣቱ ሲያወሩ  አገኟቸውና የሆነውን ተረኩላቸው። ከቁጥር 36-39 ያለውን በቀጥታ እናንብበው፤ 36-39፥ ይህንም ሲነጋገሩ ኢየሱስ ራሱ በመካከላቸው ቆሞ፦ ሰላም ለእናንተ  ይሁን አላቸው። ነገር ግን ደነገጡና ፈሩ መንፈስም ያዩ መሰላቸው። እርሱም፦  ስለ ምን ትደነግጣላችሁ? ስለ ምንስ አሳብ በልባችሁ ይነሣል? እኔ ራሴ እንደ  ሆንሁ እጆቼንና እግሮቼን እዩ፤ በእኔ እንደምታዩት፥ መንፈስ ሥጋና አጥንት  የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ አላቸው። 

መንፈስ ሥጋና አጥንት የለውምና እኔን ዳስሳችሁ እዩ። ቀደም ሲል ባየነው በዘፍ. 2፥ 23 አዳም ምን አለ? አዳምም አለ፦ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት፥ ሥጋም ከሥጋዬ  ናት፤ እርስዋ ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል። ሔዋን አጥንትና ሥጋ ነበራት፤ አጥንትና ሥጋዋም የተሠራው ከአዳም ነው፤ ስለዚህ፥ ሔዋን ሥጋና አጥንት ከነበራት  ወይም ስለነበራት መንፈስ አይደለችም። ሥጋና አጥንቷ የተገኘው ደግሞ ከአዳም  ከሆነ፥ አዳም ሥጋና አጥንት አለውና እርሱም መንፈስ አይደለም። ሰው መንፈስ ነው  የሚሉ ሰዎች የሚፎርሹት ገና ከመጀመሪያው፥ ከፍጥረትም ጅማሬ ነው ማለት ነው። 

ከኛ ከራሳችን ማንነት ተነሥተን ወደ ኋላ በመሄድ እነአዳምን እንፈትሽ ካልን፥  እነአዳም ሲፈጠሩ ከኃጢአትና የኃጢአት መዘዝ ከሆነው ነገር ሁሉ በቀር ልክ እንደ  እኛ ያሉ ናቸው። እኛ ሥጋ አለን? አዎን፤ አለን። አጥንትስ አለን? በእርግጥ አለን። 

ካልካድን በቀር። እኛ ሥጋና አጥንት፥ ሥጋና ደም የሆንን ሰዎች ነን፤ ስለዚህ  መናፍስት አይደለንም። እኛ መናፍስት ያልሆንነው እነ አዳምም መናፍስት ስላልነበሩ  ነው። ስለዚህ ሰው ምንድርን ነው? ሰው ሰው ነው። ሰው፥ ሰው ነው።

መንፈስስ ምንድር ነው? 


መንፈስ የሚለው ቃል በብሉይ ኪዳን ብዙ ተጠቅሷል። የእግዚአብሔር መንፈስ፥  መንፈስ ቅዱስን ያሳያል። መላእክትን እና አጋንንትን ወይም ርኩሳን መናፍስትንም  ያመለክታል። የሰውን መንፈስ ወይም በሰው ውስጥ ያለውን መንፈስም ያሳያል።
 
እዚህ የምንካፈለው ስለ ሰው መንፈስ ስለሆነ እሱ ላይ እናተኩራለን።  ሰው መንፈስ እንዳለው እንጂ ሰው መንፈስ መሆኑን የሚናገር ትምህርት በብሉይ  ኪዳን ውስጥ አይገኝም። የሰው መንፈስ የሰውን ውስጣዊ ማንነትም ያሳያል፤ መዝ.  51፥10 አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ። ይላል። 

እዚያው ቁጥር 17 የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና  የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም። ይላል። ሁለቱም መንፈስና ልብ  በተመሳስሎት ተጣምረው፥ አንዱ ሌላውን በሚገነባ አጻጻፍ ቀርበዋል። 

ብሉይ ኪዳን ስለ ሰው መንፈስ ይናገራል፤ ሲናገር ግን በሰው ውስጥ ስላለ መንፈስ  እንጂ ሰው ራሱ መንፈሱ መሆኑን አይናገርም። የማይናገረው ደግሞ ቃላት አጥረውት  ወይም አፍሮ አይደለም። እውነቱ ያ ስለሆነ እንጂ! ለምሳሌ፥ ምሳ. 20፥17 የሰው  መንፈስ የእግዚአብሔር መብራት ነው የሆዱን ጕርጆች ሁሉ የሚመረምር። ሲል፥  መንፈስ ሰው መሆኑን ወይም ከሰው ጋር እኩል ነገር መሆኑን ሳይሆን በሰው ውስጥ  የሚገኝ መሆኑን አመልካች ነው። 

ሌሎችም በርካታ ስፍራዎች ይህን ያሳያሉ፤ መንፈስህ (ያንተ መንፈስ) በእኔ ላይ ሁለት  እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ፤ የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል፤ የአሦርን  ንጉሥ የፎሐን መንፈስ፥ የአሦርንም ንጉሥ የቴልጌልቴልፌልሶርን መንፈስ አስነሣ፤  የቂሮስን መንፈስ አስነሣ፤ እግዚአብሔርም የይሁዳን አለቃ የሰላትያልን ልጅ የዘሩባቤልን መንፈስ፥ የታላቁንም ካህን የኢዮሴዴቅን ልጅ የኢያሱን መንፈስ፥  የቀሩትንም ሕዝብ ሁሉ መንፈስ አስነሣ፤ ወዘተ፥ ሲል ኤልያስ፥ ፎሐ፥ ቂሮስ፥  ዘሩባቤል፥ ወዘተ፥ ሰዎቹ ናቸው፤ መንፈሱ የሰውየው ወይም በሰውየው ውስጥ ያለው  ነው። የእገሌ በሚለው ውስጥ ‘የ’ የሚለው አመልካች ባለቤቱን የሚያሳይ ነው። 

ሰውየው ራሱ መንፈስ መሆኑን ሳይሆን መንፈሱ የሰውየው መሆኑን አመልካች ነው። 

ሰው መንፈስ መሆኑን ብሉይ ኪዳን አይናገርም። 
ብሉይ ኪዳን ማለት እኮ ሰው የተፈጠረበት ታሪክ ያለበት የመጽሐፍ ቅዱሳችን ክፍል  ነው። በዚያ የፍጥረት መጽሐፍ ሰው መንፈስ መሆኑን ሳይሆን መንፈሱ በሰው ውስጥ  ያለ ወይም የሚገኝ መሆኑን ነው የምናገኘው። ሰው መንፈስ ቢሆን ኖሮ ብሉይ ኪዳን  አሳምሮ፥ ሳይንተባተብና የዘንድሮዎቹ መጥተው እስኪፈቱልን ምስጢርና ድብቅ  አድርጎ አሽጎ ሳያስቀምጥልን፥ በግልጹ ቋንቋ ሰው መንፈስ ነው ይለን ነበር። ብሉይ ኪዳን ግልጽ ነው። 


ጥቂት ጨምረን ለማየት፥ ዳን. 7፥15 በእኔም በዳንኤል በሥጋዬ ውስጥ መንፈሴ  ደነገጠች፥ የራሴም ራእይ አስቸገረኝ። ይላል። ይህ የመንፈስን መገኛ ያሳያል። ዘካ. 12፥ 1 ደግሞ፥ ስለ እስራኤል የተነገረ የእግዚአብሔር ቃል ሸክም ይህ ነው። ሰማያትን  የዘረጋ፥ ምድርንም የመሠረተ፥ የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ እግዚአብሔር  እንዲህ ይላል፦ ይላል። የሰውንም መንፈስ በውስጡ የሠራ! እንግዲህ የሰው መፈጠር 
ታሪክ መገኛ የሆነው ብሉይ ኪዳን የሰውን መንፈስ እንዲህ ነው የሚገልጠው። 

በብሉይ ኪዳን አንዴም ሰው ሰው ብቻ እንጂ መንፈስ መሆኑ አልተጻፈም። የሰው  መንፈሱ በውስጡ የሚገኝ የማንነቱ ክፍል ነው።  በአዲስ ኪዳንም ሰው መንፈስ ነው ተብሎ አልተነገረም። ሮሜ. 1፥9 በልጁ ወንጌል በመንፈሴ የማገለግለው እግዚአብሔር ምስክሬ ነውና፤ ይላል፤ ‘በ’ የሚለው አያያዥ የሚያሳየው ሰው እራሱ መንፈስ መሆኑን ሳይሆን  መንፈስ በሰው ውስጥ ያለ መሆኑን ነው።  1ቆሮ. 2፥11 በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው  ማን ነው? እንዲሁም ደግሞ ከእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ለእግዚአብሔር ያለውን  ማንም አያውቅም። ሰው መንፈስ ሳይሆን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ ነው የሚለን። 

በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ሲል፥ ‘ከ’ የሚለው አያያዥ የሚያሳየው  ሰው እራሱ መንፈስ መሆኑን ሳይሆን መንፈስ በሰው ውስጥ ያለ መሆኑን ነው። 

2ቆሮ. 2፥12 ስለ ክርስቶስም ወንጌል ወደ ጢሮአዳ በመጣሁ ጊዜ፥ ለጌታ ሥራ በር  ምንም ቢከፈትልኝ፥ ቲቶን ወንድሜን ስላላገኘሁት መንፈሴ ዕረፍት አልነበረውም። 

መንፈሴ ሲል የእኔ መንፈስ ማለቱ ነው። በውስጤ ያለው መንፈስ ማለቱ ነው።  መንፈሱ እርሱ መሆኑን ሳይሆን መንፈሱ በውስጡ፥ በሰውየው ውስጥ መኖሩን ነው  የሚናገረው።  1ተሰ. 5፥23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም  ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። ጳውሎስ በጻፈበት ቋንቋ ይህ አሳብ፥ ሁለንተናችሁና ሙሉ በሙሉ ወይም  ፈጽሞ የሚለው አብረው ነው የተጻፉት። ሁለመናችሁ ምንም ሳይቀር ማለት ነው። 

ይህ የሚያሳየን መንፈስ፥ ነፍስ እና ሥጋ፥ ‘ሁለንተናችሁ’ የተባለው የሰው ማንነት ውስጥ የተካተቱ ክፍሎች መሆናቸውን እንጂ ሰው መንፈስ መሆኑን ነፍስ ያለውና  በሥጋ ውስጥ የሚያድር መሆኑን አያሳይም።

የስሕተቱ ምንጭ 


ወደ ስሕተቱ ትምህርት መግለጥ እንለፍ። ታዲያ ይህ ሰው መንፈስ ነው የሚል ትምህርት ከየት መጣ? ለምንስ መጣ? ከላይ ይህ ስሕተት ሰዎች የራሳቸው የማደጎ  ልጅ ያደረጉት የስሕተት ትምህርት ነው ብያለሁ። በምዕራቡ ዓለም ይህ ስሕተት የቆየ ነው። ብዙ አሥርታት አስቆጥሯል። በአገራችንም ዓመታት አስቆጠረ። ስር ሳይይዝ ጠወለገና የጠፋ መሰለ እንጂ ቀደም ሲል ዘሩ የተዘራበት ጊዜ ነበረ፤ ይህንን ኋላ  አነሣዋለሁ። 
በምዕራቡ ዓለም በአንድ ከረጢት ውስጥ የታጨቁ በሽተኛ የሆኑ የከፉ ትምህርቶች  አሉ። ከረጢቱ የቃል-እምነት፥ ወይም ቃለ እምነት ወይም Word of Faith ይባላል።  

ቃለ እምነት፥ ቃልም ያልሆነ፥ እምነትም ያልሆነ መርዝ ነው። በሽታ ነው፤ ደዌ።  የሚቀበሉት ሰዎችም መንፈሳዊ ድውያን ናቸው። ቃለ እምነት የሚሉት ነገራቸው፥  ‘ቃልህ አምነህ ካልከው፥ የፈለከውን ነገር መፍጠር ይችላል። እግዚአብሔርም ራሱ  እንኳ የፈጠራቸውን ፍጥረታት ሲፈጥር ቃሉ እንደሚፈጥር ያምን ነበር፤ እምነት  ነበረው፤’ ይላሉ። እግዚአብሔርም እንኳ በቃሉ ላይ ይታመን ነበር ይሏችኋል! 

ይታያችኋል? እግዚአብሔር ሲታመን! መታመን በሌላ ከራስ በላይ በሆነ ነገር መደገፍ ነው። እግዚአብሔር በሌላ ከእርሱ በበለጠ ነገር ሲታመን ይታያችኋል?  

የቃለ እምነት ስሕተትን የብልጽግና ወንጌል ደግሞ ይሉታል። በእውነቱ፥ የብልጽግና  ወንጌል የስግብግብነት ወንጌል ወይም gospel of greed ተብሎ ትክክለኛ ስም በተፈጠረበት በምዕራቡ የተሰጠው ስሕተት ነው። እኔ፥ ‘የሰብስቤነት ወንጀል’ ብዬ  ነው የምጠራው። እነሱ የብልጽግና ወንጌል ይሉታል እንጂ ይህም ከሁለቱም የጸዳ  ደዌ ነው፤ ብልጽግናም የለበትም፤ ወንጌልም የለበትም። ልክ ያኛው ቃልም እምነትም  እንደሌለበት። እርግጥ ነው፥ አንርሳ፥ የሚበለጽጉ አሉ፤ አካባቾቹ፥ ሰብሳቢዎቹ፥ ሰብስቤዎቹ ይበለጽጋሉ። አገራችን በቅርብ የተፈለፈሉትን ብንወስድ፥ ለቤታቸው  ኪራይ 70 ሺህ በወር ይከፍላሉ፤ ለሚስቶቻቸው የ10 ሚሊየን ብር መኪና ልክ  ከግሮሰሪ ማርማላታ እንደሚገዙ ይገዛሉ፤ ሁለት ዓመት ቀረጥ ባልተከፈለበትና 
ባልተፈተሸ ገንዘብ የ100 ሚሊየን ብር ቤት ይገዛሉ። እነዚህ የአገራችን ጉዶች ናቸው። 

አሜሪካ ያሉት ቤት ሰልችቷቸው የመንሸራሸሪያ መርከብና የግል አውሮፕላን ይገዛሉ።  ሕዝብ ሕዝብ እንዳንሸት ብለው ነው ይህንን የሚያደርጉት። ሕዝብ ሕዝብ  እንዳይሸቱ! ኬነት ኮፕላንድ ከአንድ ብጤው ጋር ሲያወራ እንደዚያ ነበር ያለው፤  ከbunch of demons ጋር አብረን መጓዝ የለብንም። ከአንድ መንጋ ዲያብሎሶች ጋር  አብረው እንዳይጓዙ፥ በግል አውሮፕላን ይበርራሉ። በለጸጓ! ምን ያድርጉ! ለነገሩ  አጋንንቱን ፈርተው ሳይሆን እዚያ አውሮፕላን ውስጥ የጌታ ልጆች የሆኑ ቅዱሳን  ስለማይታጡ፥ ያንን ስለሚፈሩ ነው። የብልጽግና ወንጌል ይሉታል። ‘የብልጽግና  ወንጌል’ ወይም የብልጽግና ወንጀል ያበለጽጋል፤ ሰብስቤዎቹን።  

‘የጤንነት ወንጌል’ ደግሞ ይሉታል። ቃለ እምነት፥ የብልጽግና ወንጌል፥ የጤንነት  ወንጌል። መልከ ጥፉን በስም መደጋገፍ ያውቁበታል። ስንቱን መድኃኒት እያስጣሉ፥  እየገደሉ፥ ለሞት እየዳረጉ የጤና ወንጌል! ደግሞ እኮ፥ ራሳቸውም ይታመማሉ፤ እነዚህ  መናፍስት ነን የሚሉትም ሳይቀሩ አንዳንዴ ይሰበራሉ፤ በጄሶ በፋሻ ታስረው ይታያሉ፤ ደፈር የሚሉት ናቸው የሚታዩት። እንጂ ብዙኃኑ ተደብቀው ነው የሚታከሙት። 

ሰብስበው የበለጸጉቱ ላለመታየት እውጭ እየሄዱ ይታከማሉ። መንፈስ እኮ ቢሆኑ  ኖሮ መንፈስ የሚታመም ነገር የለውምና ይህ ችግራቸው ባልሆነም ነበር። ሲታመሙ  የሚደበቁትና መታመማቸውን የሚክዱት ስለሚያፍሩ ነው።  

ሰው ሰው ነውና በኃጢአት ከወደቀ በኋላ የተከሰቱት መዘዞች ሊያገኙት ይችላሉ።  ከነዚህ መዘዞች ዋናውና ትልቁ ሞት ነው። ወደ ሞት የሚወስደው ጎዳናው ደግሞ  ብዙ ነው። ማርጀትም ራሱ የውድቀት መዘዝ፥ የኃጢአት ጠንቅ ነው። ወረርሽኞችም፥  ሕመሞችም፥ አደጋዎችም ሊከሰቱ ይችላሉ። ማንም ሰው ከዚህ አያመልጥም፤  በተለይም ከሞት፤ እንደ ኤልያስ ወይም እንደ ሄኖክ ካልተነጠቀ በቀር። ለምን? ሰው ነዋ! የጤንነት ወንጌልም እንደ ብልጽግና ወንጌል ነው፤ ጤንነትም ወንጌልም የሌሉበት  በሽታ ነው።

‘ሰው መንፈስ ነው’ በአገራችን ሲጀመር እና ዛሬ 


ወደ ሰው መንፈሶቹ ስንመጣ፥ ይህንን ችግረኛ፥ ችግረኛ አይደለም በሽተኛ ትምህርት  በአገራችን ከልጅ እስከ አዋቂ፥ በልጅነትም፥ በጅልነትም፥ በአውቆ አበድነትም የዘሩት ጥቂት አይደሉም። 

"ዱሮ ሰው መንፈስ አይደለም፤ ሰው መንፈስ ነፍስና ሥጋ ነው ብዬ አስተምሬ ነበር። ዱሮ እዚህ ኢትዮጵያ የነበርኩ ጊዜ ማለት ነው። ስለዚህ ባወቅሁ ጊዜ አሳቤን ቀይሬአለሁ፤ አሁን ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ ሥጋ ውስጥ ያድራል ብዬአለሁ።" ኃይሉ ዮሐንስ።

“ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ነው ሚኖረው።” ዶ/ር ቶሎሳ ጉዲና። 

ዱሮ ኢትዮጵያ የነበረ ጊዜ ሰው መንፈስ፥ ነፍስ፥ ሥጋ ነው ያለው ኃይሉ ዮሐንስ ወደ  አሜሪካ ከሄደ በኋላ ይህን ትምህርት ከየት አገኘው? ግልጽ ነው፤ ከአሜሪካ ነው  ያገኘው። አሜሪካ ውስጥ ይህን የሚያስተምሩ ሰዎች ይኖሩ ይሆን? የተወለደውስ የት ሆነና!? ኃይሉ በአንድ ወቅት እንደ መንፈሳዊ አባቱ እንደሚያየው የተናገረለት ኬነት  ኮፕላንድ የዚህ አስተማሪ ነው። ስለዚህ የዚህ የኃይሉ ዮሐንስ፥ ‘ሰው መንፈስ ነው’  ትምህርት ምንጭ ኮፕላንድ ነው ማለት ነው። ኬኔት ኮፕላንድ ደግሞ ትምህርቶቹን  የኮረጀው ከኦራል ሮበርትስ እና ኬኔት ሄግን ነው። 

እንደ Word of Faith ወይም የቃል እምነት ትምህርት አባት የሚቆጠረው Kenneth  E. Hagin, Man on Three Dimensions በተባለው መጽሐፉ ገጽ 8 እንዲህ ብሏል፤  Man is a spirit who possesses a soul and lives in a body. 

Man's spirit is that part of him that knows God. He is in the  same class with God because God is a Spirit and God made  man to fellowship with Him. God made man for His own  pleasure. Man is not an animal. In order to fellowship with  God, man must be in the same category with God. Therefore,  just as God is Spirit, so is man spirit.1 የዚህ ጥቅስ የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር፤ Man is a spirit who possesses a soul  and lives in a body. ይላል።

 ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ፡ ያድራል ወይም ይኖራል ማለት ነው። ይህ ቀመር የኛዎቹ የፈጠሩት አይደለም።  የኮረጁት ነው። ሄግን ራሱ ትምህርቱን ያገኘው ከE. W. Kenyon ነው። ኬንየን ከሞተ  ከ21 ዓመታት በኋላ በልጁ አማካይነት ተሰባስቦ በታተመው The Bible in the  Light of Our Redemption በተባለ መጽሐፉ ገጽ፥ 17-18 እንዲህ ይላል፤

 
The spirit is the real man, created in the image of God . . .  Your body is not you. Your mind is not you. You have a mind which you use. You possess a body which you use.  Your mind and body are merely the instruments of your  spirit, the real YOU.2 እንደ ኬንየን ትምህርት፥ ‘the real YOU’ ያለው እውነተኛው ሰው መንፈስ ነው። 

ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ የዚህ መገልገያዎች ናቸው። በአገራችን ይህንን የተለከፈ ትምህርት የሚያስተምሩ ሌሎችም አሉ። ከአዲሶቹም  ከቆዩትም። ፓስተር ቄስ ዶክተር ቶሎሳ ጉዲና፥ በብስራት ብዟየን ጉባኤ፥ ‘ሰው  መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው በሥጋ ውስጥ ይኖራል’ ሲሉ፥ የጉባኤው ጠቅላላው ፉጨትና ጭብጨባ እንዴት እንዳስተጋባ ያስገርማል። ‘ለምን ጭብጨባ አስተጋባ?’  ተብሎ ቢጠየቅ፥ ‘ይኸው አንጋፋዎቹም ያምኑበታል! ውሪዎቹ ብቻ ሳንሆን፤ ይኸው! 

አባቶቹም ያምኑበታል፤ ፈልፈላዎቹ ብቻ ሳንሆን’ የሚል ያስመስለዋል። ይመስላል።  በእውነቱ፥ ለአንጋፋ ለአንጋፋማ እነ ኬኔት ኮፕላንድ ራሳቸውም እኮ አሉ፤ ኮፕላንድ 80ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኝ አዛውንት ነው፤ ሽማግሌ ነው፤ አንጋፋ ነው፤   እሱን ምስክር ማድረግ ይችላሉ እኮ ኃይሉ ዮሐንስ እንዳደረገው። እነ ሄግንንም እነ ኬንየንንም መጥራት ይችላሉ እኮ በሕይወት ባይኖሩም። እንዲህ ያስቦረቃቸው ከአገራችን ከቀድሞዎቹ አንድ ስላገኙ ነው። 

አዲሱ ሐዋርያዊ ዳግም ሥሪት (አሐዳስ ወይም NAR) በሚባለውን እንቅስቃሴ  ውስጥ የተተበተቡት እኮ ፓስተር ቄስ ዶክተር ቶሎሳንም ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ  አበሾችም ናቸው።

 አንዳንዶቹ ቀደምት እና ትልልቅ የሚባሉትቱ የአዳዲሶቹ ‘አባቶችና’ ወርሃዊ ተቆራጭ የሚሰጣቸው ተከፋዮች ናቸው። በሥርዓት ‘አባት’ ወይም አሠልጣኝ፥ mentor እየተባሉ አሥራት የሚከፈላቸው ተጧሪዎችም አሉ። ከፋዮቹ  ደግሞ የውስጥ ነገራቸው ውስጥ እየገቡ እንዳያምሷቸው በጣም አያቀርቧቸውም፤  በገደብ ያርቋቸዋል፤ እነዚያም ክፍያዋ እስካልቀረች ድረስ አይጫኗቸውም። አንዳንዶቹ  ደግሞ አሠልጣኝ ሳይሆኑ ለዕለት የሚሆን ዘይት ይዘው የሚዞሩ ቀቢዎች ናቸው። እነሱም ተከፋዮች ናቸው። ሌሎች ደግሞ በአደባባይ አይናገሩም፥ አይጽፉም፥  አያሠለጥኑም፥ አይቀቡም እንጂ ያምኑታል። ብቻ እንደዚህ እንደ ፓስተር ቄስ ዶክተር  ቶሎሳ በመድረክ፥ በአደባባይ፥ በድፍረት ራሱን የሚገልጥ አንድ ሲገኝ ያስቦርቃል፤  ያስፈነድቃል። እና እነ ብስራት እና ጉባኤው ቢፈነድቁ አያስገርምም።

በአገራችን፥ 'መንፈስ ነን' የሚሉ ሰዎች በኛ አቆጣጠር በ1970ዎቹ መጨረሻና 80ዎቹ መጀመሪያ ተነሥተው ነበር። ያኔ እኔ አዲስ ክርስቲያን ስለነበርኩ እንደዚያ የሚሉ አሉ  ሲባል ነው የምሰማው። ኋላ እኛም ቤተ ክርስቲያን ብቅ አሉ። ታዲያ እነዚህ ሰዎች  ምንም ዓይነት አካላዊ ችግር (እጦት፥ ሕመም፥ ሌላም፥) ሲገጥማቸውና ስሞታ  ሲያቀርቡ ይቀለድባቸው ነበር። ሲታመሙ መንፈስ እንዴት ይታመማል? ይባሉ  ነበር። ልብሳችን አያረጅም፤ እኛም አናረጅም፤ 120 ዓመት ነው የምኖረው ይላሉ። 

አንሞትም የሚሉም ነበሩ፤ እንዲያውም ሳልሞት እንደ ኤልያስ ነው የምነጠቀው  ያለኝም ነበረ። እየቆዩ እያረጁ ብዙዎቹ ሞቱ እንጂ!  በዚያኑ ዘመን መናፍስት ስለሆኑ አንሞትም ከሚሉትና ሞትን ከሚክዱት መካከል  አንዱ በአዋሳ የክብሩ ወንጌል የሚባል ቤተ ክርስቲያን መጋቢ የነበረ ሰው ነው። ይህ ሰው የገዛ ልጁ ሲሞትበት የሚክደው ሞት እቤቱ መግባቱ እንዳይታወቅ በድኑን እንደ  ዕቃ በጆንያ ጠቅልሎ ሲያሸሽ ጥቁር ውኃ የሚባለው ከአዋሳ በሰሜን የሚገኘው ኬላ  ላይ ተይዞ ነበር። በጊዜው ለክርስትና እፍረት የነበረ የናኘ ዜና ነበረ። እነዚህ ሰዎች ያኔ  ብዙም በአገራችን ከማይታወቀው ቃለ እምነት ስሕተት ሰምተውና አንዷን ቀንጭበው  ወስደው በራሳቸው እርሾ አቡክተውና አባዝተው ነበር ይህን 'አንሞትም' የሚሉትን ስሕተት የነዙት። በዚህ ትምህርት የተለከፉት ብዙዎቹ (ብዙዎቹ ሳይሆን በሙሉ  ማለት ይቻላል) የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን የሚጠየፉና የሚያንቋሽሹ፥ ከቃሉ ትምህርት የጸዱ፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብቶ መማርን የሚንቁ፥  ራሳቸውም ገብተው ያልተማሩ ሰዎች ናቸው። 

በአገራችን ይህ ‘ሰው መንፈስ ነው፤ ሰው አምላክ ነው፤ እኔና አብ አንድ ነን’ ትምህርት  እንደገናና አሁን በሚታወቅበት መልኩ የተረጨበት ዋና እና አዲሱ ቱቦ የሆነው ኃይሉ ዮሐንስ ነው። "ዱሮ ሰው መንፈስ አይደለም፤ ሰው መንፈስ ነፍስና ሥጋ ነው ብዬ  አስተምሬ ነበር። ዱሮ እዚህ ኢትዮጵያ የነበርኩ ጊዜ . . . አሁን ሰው መንፈስ ነው፤  ነፍስ አለው፤ ሥጋ ውስጥ ያድራል ብዬአለሁ።" ማለቱን ቀደም ሲል አውስቼአለሁ። ይህን ያለው፥ 'ተሳስቼ ነበር አሁን አረምኩ የምትለው ነገር አለህ ወይ?' ተብሎ  በጋዜጠኛዋ ለተጠየቀው ሲመልስ ነው። ይገርማል! ትክክለኛው ትምህርት ስሕተት፥  የተሳሳተው ደግሞ ትክክል ሲሆን የመሳትና የማሳት ምስጢር ወለል ብሎ ይታያል። 

አሐዳስ እና አምስቱ ቢሮዎች 


ሰው መንፈስ ነው የሚለው የስሕተት ትምህርት የታቆረበትና የሚንቆረቆርበት ምንጭ  አለው። ሳቾቹና አሳቾቹ ሐዋርያትና ነቢያት የሚባሉቱ በአዲሱ ሐዋርያዊ ዳግም  ሥሪት (New Apostolic Reformation - NAR) ጎርፍ ውስጥ ያሉ ሰዎች ናቸው።  ‘አምስቱ ቢሮዎች’ ብለው የሐዋርያትና ነቢያትን አገልግሎት የሚያደናንቁና  የሚያራግቡት፥ የሚሉቱና የሚያስብሉቱም ናቸው። The Five-fold Ministryም  ይባላል። እዚህ ላይ ይህን ነጥብ እናንሣ፤ ለምን አምስት ሆነ? የአምስቱ ቢሮዎች  የንግድ ፈቃዷ ከኤፌ. 4፥11 የተወሰደችው ናት። ለምን ከሮሜ 12፥6-8 ተወስዶ ሰባቱ  አልሆነም? ወይም እንደ 1ቆሮ. 12፥8-9 ለምን ዘጠኝ ወይም እንደ 1ቆሮ 12፥28 ለምን  ስምንቱ ቢሮዎች አልሆኑም? አንድ ሰው አንድ ነገር ከጀመረ ያንን ማስተጋባት  የተለመደው ዘዬ ነው። አንድ ሰው አምስቱ ቢሮዎች ብሎ ጀመረ ከዚያ ሌሎቹ  ማስተጋባት ነው። 

አምስቱ ቢሮዎች የሚለው ነገር የተጀመረው ከአዲሱ ጴንጤቆስጣዊነት (Neo Pentecostalism) ወዲህ ከመንግሥታሁን (Kingdom Now) እና የግዛት ስነ  መለኮት (Dominion Theology) ጋር ተቆራኝቶ ነው። እነዚህ አምስቱ፥ በተለይም  ከአምስቱ ሁለቱ ሐዋርያትና ነቢያት የዘመናዊቷ ቤተ ክርስቲያን መሠረት ተደርገውም  እስከ መቆጠር ደርሰዋል። አንድ መርሳት የሌለብን ነገር፥ የቀድሞው መሠረት  እንዳልተፈረከሰና አሁንም በቦታው ያለ መሆኑን ነው። አዲስ መሠረት  አይመሠረትም። በመሠረቱ ላይ እናንጻለን፥ እናጸናለን እንጂ አዲስ የሐዋርያትና    የነቢያት መሠረት አንመሠርትም። መሠረቱ ቀድሞውኑ ተመሥርቶአል።

  የዘመናችን ሐዋርያትና ነቢያት የስሕተት መሠረቶች ናቸው እንጂ የአዲስ ኪዳን  መሠረቱ አይደሉም። በኤፌ. 2፥20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤ የሚለው እነሱ መሠረቶቹ  መሆናቸውን ሳይሆን እነሱም ራሳቸው የተመሠረቱበት ዓለት መኖሩን የሚያሳይ ነው። መሠረቱ ተመሥርቷል፤ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደ ተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ  የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትሁ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በእርሱ  ላይ እንዴት እንዲያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። 1ቆሮ. 3፥10-11። መሠረቱ  ኢየሱስ ነው አለቀ። አይደለም ኢየሱስ ሳይሆን ነቢያትና ሐዋርያት ናቸው እንደ ኤፌ. 2፥20 ከተባለም እሱም አልቋል፤ ነቢያቱ በወከሉት በብሉይ ኪዳንና ሐዋርያቱ  በወከሉት በአዲስ ኪዳን ላይ ተመሥርተናል። የዘመናችን ሐዋርያትና ነቢያት የስሕተት መሠረቶች ናቸው እንጂ የአዲሱ ኪዳን መሠረቶች አይደሉም።  

የ‘ሰው መንፈስ ነው’ ትልልቅ አደጋዎች
 

ቀደም ሲል፥ ‘ሰው መንፈስ ነው’ የሚለው ጥያቄ ሞኝ ጥያቄ እንደሚመስልና ግን የግድ አንዳንድ ሞኝ ጥያቄዎች መቅረባቸውና መልስ መሰጠቱም አስፈላጊ መሆኑ ግድ መሆኑን እና ጥያቄው እንዲነሣ አስገዳጅ የሆነው የተሳሳተው የቃለ እምነት የስሕተት ስነ ሰብእ (Word of Faith Anthropology) መሆኑን አየን። ጤናማው ትምህርት ሰው ሰው መሆኑና እግዚአብሔር በስድስተኛው ቀን የፈጠረው መንፈስን ሳይሆን ሰውን መሆኑን፥ አዳምና ሔዋን መናፍስት ሳይሆኑ ሰዎች መሆናቸውን፥ ሰው መንፈስ  ወይም መንፈስ ሰው አለመሆኑን አየን። ሰው መንፈስ መሆኑን የሚያሳይ አንድም የብሉይ ኪዳን ክፍል አለመኖሩን እና መንፈስ በሰው ውስጥ የሚኖር የማንነቱ ክፍል  መሆኑን የሚያሳዩ በቂ ጥቅሶችን አይተናል። የስሕተቶቹን ምንጭ ስንመረምርና  ስንፈትሽ ስሕተቱ የተወለደው በአሜሪካ መሆኑን፥ የቃለ እምነት አስተማሪዎች የነዙትትምህርት መሆኑን፥ ከኬንየን ወደ ሄግንና መሰሎቹ፥ ከነሄግንና መሰሎቹ ወደ  ኮፕላንድና መሰሎቹ፥ ከኮፕላንድና መሰሎቹ ወደ የኛዎቹ ኃይሉ ዮሐንስና መሰሎቹ  የመጣ ድውይ ትምህርት መሆኑን አይተናል። 

ቀጥሎ ይህ፥ ‘ሰው መንፈስ ነው’ የሚለውን ስሕተት ሁለት ትልልቅ አደጋዎች እንመልከት፤ 

አደጋ አንድ፤ መንፈስ ስለሆንን አንረክስም 


የመጀመሪያው አደጋ፥ ‘ሰው መንፈስ ከሆነ በሥጋው ከሚያደርገው ርኩስት መንፈሱ   የታተመች ናትና አያገኛትም፤ አትረክስም።’ የሚል ግንዛቤ ነው። ይህንን አንዳንዶቹ አያስተምሩትም። አንዳንዶቹ ደግሞ በገሃድ አያስተምሩትም፤ በተግባር ግን ይኖሩታል፤ ያደፋፍሩታልም። ሲያፋጥጧቸውም ፈጽሞ አያምኑትም። ገና ከመጀመሪያው ምዕት  ዓመት ጀምሮ የነበረ ግኖስቲሲዝም የተባለ፥ ሥጋና ነፍስን ወይም ሥጋና መንፈስን  (አካላዊና መንፈሳዊውን ማንነት ማለት ነው) ነጣጥሎ በማየትና በማሳየት የሠለጠነ ትምህርት ነበረ። አካላዊውን ክፉ፥ ረቂቁንና የማይታየውን በጎ የማድረግ፥ ሰውን በተመለከተም ሥጋን ርኩስ፥ ነፍስና መንፈስን በጎ የማድረግ ትምህርት ነው። ግኖስቲኮች ለተለያዩ ነገሮች የየራሳቸው ትምህርቶች አሏቸው፤ ከተርታው፥  ከመደዴው ሰው የላቀ ልዩ እውቀትን የተቀዳጁ እንደሆኑም ያስተምራሉ። 

ግኖስቲኮች ሰውን በተመለከተ ትምህርታቸው፥ መለኮታዊው ብልጭታ ወይም መንፈስ በዚህ ቁሳዊው፥ ሥጋዊው አካል ውስጥ ሆኖ፥ ልክ ግዞት ቤት ወይም መኅኒ  ቤት ውስጥ እንዳለ ሆኖ ተጠምዶ፥ ታግቶ፥ ታስሮ ተቀምጧል፤ ከዚህ ክፉ ግዞት ወይም ወኅኒ ቤት ውስጥ ሊወጣም ይጥራል፤ የሚል ዓይነት ነው። እንደ  ግኖስቲሲዝም ትምህርት ነፍስና መንፈስ መልካም፥ ሥጋ ርኩስ ናቸው። በዚህም  ኃጢአትን የሥጋ ብቻ የማድረግ አባዜ አላቸው። 

ከላይ እንዳልኩት የዘመናችን አዲሶቹ ግኖስቲኮች የኃጢአት ልቅነትን አንዳንዶቹ  አያስተምሩም፤ አንዳንዶቹ በገሃድ አያስተምሩትም፤ ግን የሚያስተምሩቱ ሰዎች ወይም  የሚያስተምሯቸው ሰዎች አመላለሳቸው ትምህርታቸውን ይገልጠዋል። 1ኛው  የዮሐንስ መልእክት የተጻፈው ለዚህ ኑፋቄ፥ ለሁለቱም ዘርፎች ስሕተቶች ምላሽ  እንደሆነ ይታመናል። በ1ኛ ዮሐንስ ውስጥ ዮሐንስ እነዚህን ሁለት ነገሮች፥ እውቀት ስለሚሉት ነገርና ኃጢአትን በተመለከተ አሳምሮ ነው የጻፈባቸው። እውቀት አለን  እያሉ እንዳይኩራሩና ኃጢአትን ደግሞ እተተዳፈሩ እንዳያደርጉ፥ እንዳይለማመዱ  አጥብቆ ያሳስባቸዋል። እነዚህን ሁለት ቃላት እውቀት ወይም ማወቅ እና ኃጢአት የሚሉትን ቃላት በዚህ መልእክት ውስጥ ብንፈትሽ በሰፊው የተነገረበት ጉዳይ ሆኖ  እናገኛለን። 

ሰው መንፈስ ነው የሚሉ ሰዎች አደገኛ ትምህርት መንፈስ ስለሆንን በሥጋ ለሚደረግ  ኃጢአት ፈቃድ የመስጠት ዝንባሌ ነው። ይህ ሥጋን ቀፎ ወይም ጊዜያዊ አድራሻ ብቻ  አድርጎ ማስተማር አንዳንዶቹን የቃል-እምነት ተከታዮች ሰውነት ማደሪያ ብቻ ነው፤  ተሸካሚ ብቻ ነው፤ ድንኳን ብቻ ነው፤ ጊዜያዊ መጠለያ ብቻ ነው፤ የምንቆሽሽበት  ቱታ ነው፤ በቱታው ሆነን ስንንደባለል ሥጋችን አይቆሽሽም ይላሉ። በሥጋ  የምናደርገው ኃጢአት ሥጋችንን ያረክሰዋል፤ ነፍሳችንን አይበክላትም፥ በተለይም  መንፈሳችንን አይነካትም፤ መንፈሳችን ለቤዛ ቀን የታተመች ናትና አትገኝም፤  አትደረስም፤ ወደሚል የድፍረት ኃጢአትም ይጋብዛቸዋል። ኃጢአትን ይዳፈራሉ፤  ያዳፍራሉ። ይህ የዚህ ጠማማ ትምህርት አንድ መዘዝ ነው። በአደባባይ ቢያስተምሩት  በገሐድ ስለሚወገዙ በተግባር ነው ሌሎች ለቀቅ፥ ፈታ ዘና ያለ ሕይወታቸውን  ምሳሌነት በማየት የሚከተሏቸው። 

ይህ ግን ለቀቅ ማለት ሳይሆን ልቅ መሆን ነው። ፈታ ዘና ማለት ሳይሆን ስድ መሆን ነው። 2ጴጥ፣ 2፥18-19 ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥  በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ። ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው፦ አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤  ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና። የሚለው የነዚህን ዓይነት ሐሰተኛ  አስተማሪዎች ነው። ዓለምንና ሥጋን የማይሰናበቱ ብዙ ወጣቶች በቀላሉ  የሚከተሏቸው በዚህ የወረደ ልቅ የአኗኗር ዘይቤያቸው እየተሳቡ ነው። እነዚህ ሰዎች  ዓለምን ስለመካድ፥ ለሥጋ ፈቃድ ስላለመገዛት፥ ስለ ቅድስና፥ ራስን ስለመካድ፥  መስቀልን ስለመሸከም፥ ስለ ደቀ መዝሙርነት፥ ስለ ኃጢአት፥ ወዘተ፥ የማይሰብኩት  ስለዚህ ነው። 

እርግጥ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሥጋችንን ማደሪያና ቤተ መቅደስ ይለዋል፤ ድንኳንም  ይለዋል፤ ያ ማለት እንደ ሜካኒክ ቱታ ነው ማለት ግን አይደለም። ሜካኒክ ቀኑን ሁሉ  ሲሠራ ውሎ ቱታው ቆሽሾ የውስጥ ልብሱ ሳይቆሽሽ፥ ወይም አካሉ ሳይቆሽሽ ወደ  ቤቱ ሊመለስ ይችላል። ኃጢአት ግን በሥጋ ይገለጣል እንጂ ምንጩ ሥጋ አይደለም። 

ከውስጥ ከልብ ነው የሚመነጨው። ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፥ ነፍሰ  ገዳይም የሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት በእርሱ እንዳይኖር ታውቃላችሁ። 1ዮሐ. 3፥15።  ቱታ አይጠላም፤ የሚጠላው ከቱታው በታች ያለው ማንነት ነው። ልብ የሚባለው  ነገር ነው። ማቴ 5፥28 እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ  በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል። ካለ ከማመንዘር በፊት የሆነ ነገር አለ። ማየትና  መመኘት። ቱታ አይመኝም። የሚመኘው ከቱታው በታች ያለው ማንነት ነው። 

ስለዚህ ሥጋ የሜካኒክ ቱታ አይደለም።  

ኃጢአት ከቱታ ወደ ሰውነት ሳይሆን እንዲያውም ከሰውነት፥ ከውስጥ፥ ከልብ ወደ  ቱታው የሚመጣ ነገር ነው። ማር. 7፥20-23 እርሱም አለ፦ ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው። ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ አሳብ፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ መጐምጀት፥ ክፋት፥ ተንኰል፥ መዳራት፥ ምቀኝነት፥ ስድብ፥ ትዕቢት፥ ስንፍና ናቸውና፤ ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል ሰውን ያረክሰዋል። ይላል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ከውስጥ መንጭተው በተግባር በአካልና በሥጋ  ይገለጣሉ። የቱታው መቆሸሽ ብቻ ሳይሆን ቱታውንም የሚያረክሰው ጉዳይ ነው ጉዳዩ። ‘ከሰው ልብ የሚወጣ’ ብሎ ይጀምርና፥ ‘ሰውን ያረክሰዋል’ ብሎ ይጨርሳል። 

ስለዚህ ኃጢአት የሚኖረው በምናችን ነው ሲባል ምንጩንም መድረሻውንም መንካት  ተገቢ ነው። በሕይወት በሥጋ እስከኖርን ድረስ ኃጢአት በሁለንተናችን ሊኖርና ሁለንተናችንን  ሊበክል ይችላል። ቅድስናም እንዲሁ። 1ቆሮ. 6፥19-20 ወይስ ሥጋችሁ  ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ  በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። ይላል። ደግሞም 1ተሰ. 5፥23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። ይላል። ሥጋችን፥ መንፈሳችን፥   ነፍሳችን ነቀፋም ቅድስናም ሊኖርባቸው ይችላል። 

መጽሐፍ ቅዱስ፥ በተለይ አዲስ ኪዳን፥ ሥጋ ሲል ከአጥንትና ጅማት፥ ከደምና ሌሎች ብልቶቻችን ያለፈ ነገርን መናገሩ ነው። ለምሳሌ፥ ገላ. 5፥17 ሥጋ በመንፈስ ላይ  መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም  የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም። ሲል ወይም ኤፌ. 2፥3 በእነዚህም ልጆች  መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።ሲል የሥጋ ብልቶችን ሳይሆን ሥጋዊ አስተሳሰብን መግለጡ ነው። 

‘ሰው መንፈስ ነው’ የሚሉ አንዳንዶች ሥጋችን አይረክስም እና ኃጢአት ብናደርግም  እውነተኛ ማንነታችንን (ማለትም፥ እንደ እነርሱ ትርጉም መንፈሳችንን) አይነካምና  አንረክስም የኃጢአት የፈቃድ ወረቀት አድርገው ሊጠቀሙባት ይሞክራሉ። ነገር ግን  ይህንን ለማድረግ ሲጋብዙና ሲጋበዙ፥ ሥጋቸው ኃጢአት እንዲያደርግ ምንጫቸው  የረከሰ መሆናቸውን ከስር፥ ከውስጥ፥ ከምንጭ የሆነ መበላሸታቸውን ይመሰክራል። 

ስለዚህ ኃጢአትም ቅድስናም በምናችን ውስጥ ይኖራል? ቢባል፥ መልሱ ሁለቱም  የማያቋርጥ የመሰጠት ሂደቶች ናቸው። ለኃጢአት ከተሰጠን ኃጢአት በሁለንተናችን  ሊሰለጥን ይችላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሁለንተናችንን ሊገዛውና ሊቆጣጠረው ከሰጠነው  ሁለንተናችን ይቀደሳል። ፈቃዱ በእጃችን ነው ያለው። 

ሥጋችን ድንኳን ነው? አዎን።ድንኳን የሚሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ፥  በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘላለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንጻ  እንዳለን እናውቃለንና። በዚህ ውስጥ በእውነት እንቃትታለንና፥ ከሰማይም  የሚሆነውን መኖሪያችንን እንድንለብስ እንናፍቃለንና፤ ለብሰን ራቁታችንን አንገኝም። በእውነትም የሚሞተው በሕይወት ይዋጥ ዘንድ ልንለብስ እንጂ ልንገፈፍ የማንወድ  ስለ ሆነ፥ በድንኳኑ ያለን እኛ ከብዶን እንቃትታለን። 2ቆሮ. 5፥1-4። ግን ይህ ድንኳንና መቅደስ የቅዱሱ ማደሪያ ነውና ብልቶቻችን ለዓመጻ የጦር ዕቃ ሆነው መጠቀሚያ  መሆን የለባቸውም። በተቃራኒው ነው ቃሉ የሚያስተምረን፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ  የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ሮሜ 6፥13። 


የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ  አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን  ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ። 1ቆሮ.  3፥16-17። እናንተ ያለው ‘ቢያፈርስ’ የተባለውን የሚፈርሰውን ሥጋም ጨምሮ  ሁለመናችንን እንጂ መንፈሳችንን ብቻ አይደለም። በሌላ ቦታ ይህን ይበልጥ ግልጽ  ያደርገዋል፤ ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው  የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ። 1ቆሮ. 6፥19-20። እዚህ  ሥጋችን ነው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ የተባለው። 

ስለዚህ መንፈሳችን ታትማለች አትቆሽሽም እያሉ ኃጢአትን በግልጥም በስውርም እንደ ጨው የሚያልሱ ሰዎች ወደ እርድ ቦታ ሊወስዱን ነው። ለሌላ አይደለም።  ኃጢአት ሥጋችንን፥ ነፍሳችንን፥ መንፈሳችንንም ሁለመናችንን ነው የሚያረክሰው። 

ከዚያም ይመነጫል። ይህ ‘ሰው መንፈስ ነው’ ስለዚህ በሥጋ የሚደረግ ነገር  መንፈሳችንን፥ ማለትም እኛነታችንን አያረክስም የሚለው አሳች ትምህርት አንደኛው  አደጋ ነው።

አደጋ ሁለት፤ እኛ አማልክት ነን

 
ሁለተኛው የ‘ሰው መንፈስ ነው’ ስሕተት ትልቅ አደጋ፥ ሰው አምላክ ነው ማሰኘቱ ነው። እንዴት ነው የሚያሰኘው? ቢባል፥ እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ሰውም መንፈስ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ፥ ሰውም መንፈስ ከሆነ፥ ሰው እግዚአብሔር ነው ማለት ነው። ይህ ነው አደጋው። እኛ ትንንሽ እግዜሮች ነን፥ ትንንሽ አምላኮች ነን፥ አማልክት ነን የሚሉት ለዚህ ነው። ኃይሉ ዮሐንስ፥ እያፌዘም  ቢሆን፥ ‘ትንንሽ አይደለም፤ ትልልቅ በሚለው ይስተካከልልኝ’ ብሏል። ኃይሉ ዮሐንስ
እና የዚህ አሳች እኩይ ትምህርት ተከታዮች ማወቅ ያለባቸው የቃሉ እውነት፥ እነሱም ሆኑ ማንም ሰው ትልልቅም፥ ትንንሽም አማልክትም እንዳይደሉ ነው። እነርሱ ሰዎች  ብቻ ስለሆኑ አምላክነት ሲያምራቸው ይቅር። ጣዖት ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል እንጂ  አምላክነት አይታሰብም። አምላክ አንድ ብቻ ነው፤ የአምላክነት ቦታው ተይዟል።  ለአምላክነት የተከፈተ ክፍት የሥራ ቦታ የለም። 

እንግዲህ፥ ትንንሽም ይሁን ትልልቅ አማልክት ነን የሚሉት ከዚህ ‘መንፈስ ነን’  ከሚለው ትምህርት ጋር የተያያዘ ነው። የቃለ እምነት ትምህርት የሚሉትም  ከአምላክነት ጋር የተቆራኘ ነው። ‘እግዚአብሔር በቃሉ ከፈጠረ እኛም በቃላችን መፍጠር እንችላለን፤’ የሚል ነው። እግዚአብሔር እምነቱን ካመነ፥ እኛም  እምነታችንን ማመን እንችላለን። እግዚአብሔር ፈጣሪ፥ እኛም ፈጣሪ ነን፤ እኔና እግዚአብሔር አንድ ነን፤ እኛ የእግዚአብሔር class ነን፤ የእግዚአብሔር kind ነን፤  ይላሉ። እንጀራ አባቶቻቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ስለሆኑ ነው kind እና class  የሚሉት፥ የእግዚአብሔር ዓይነት ነን ማለታቸው ነው። ዓይነት! እግዚአብሔርን፥  ‘ዓይነት’ ሲሉት አፋቸው ተብተብ አይልም፤ አይፈሩም። እግዚአብሔር ዓይነት አይደለም። እርሱ ከብዙዎች መካከል አንዱ አይደለም። እርሱ ከብዙዎች ጋር  የሚመሳሰል አይደለም። እርሱን የሚመስል ሌላ የለም። ከማንም ጋር አይመሳሰልም፤  አይተያይም። በአምሳሉ ከፈጠረን ከኛም ጋር አይተያይም። 

‘እኛ መንፈስ ነን’ ካልን ግን ይህንን ብቻ ሳይሆን ሌላም ማለት እንችላለን፤ እኛ የእግዚአብሔር ዓይነት ነን ብቻ ሳይሆን ቀጥለን፥ እግዚአብሔር የኛ ዓይነት ነው  ለማለትም ደፋሮች እንሆናለን። ስነ መለኮቱን እንገለብጠዋለን። ሰው እግዚአብሔር  ነው ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሰው ነው ወደ ማለትም እንገለብጠዋለን። 

ሰው የእግዚአብሔር መልክ ነው ማለት መንፈስ ነው ማለት ነው? እናም፥  እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ሰውም መንፈስ ነው፤ ስለዚህ፥ ሰው እግዚአብሔር ነው  ማለት ነው? በዘፍ. 1፥26-27 እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ  ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥  በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ  ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው። ካለ ሰው  በእግዚአብሔር መልክ ተፈጠረ ስላለ በግልባጩ የእግዚአብሔር መለኪያና ትርጉም  ሰውን በማድረግ እግዚአብሔር ሰውን ይመስላል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰው ነው  ልንል ነው? በሂሳብና በግመታ ሳይንስ Extrapolate ማድረግ ወይም Extrapolation  የሚሉት ነገር አለ። ግራፍን ወይም ቁጥርን አስረዝሞ ቀጣዩን መልክ ማሳየት ማለት  ነው። በዚህ ሰው መንፈስ ነው በሚለው የስሕተት ትምህርት ላይ ያንን ስናደርግ  ወይም ብናደርግ የምናገኘው ይህ ነው። ሰው መንፈስ ነው ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ሰው ነው ወደሚል ድምዳሜ ያደርሰናል። 


ጠማማው የቃል-እምነት ትምህርት፥ 'እግዚአብሔር መንፈስ ነው፤ ሰው  የእግዚአብሔር መልክ ከኖረውና እግዚአብሔር መንፈስ ከሆነ ሰውም መንፈስ ነው  ማለት ነው።' የሚል ነው። የዚህ የቃል-እምነት ትምህርት አካሄድ ግብ ያ ነው። ግን  ከዘፍ. 1 ወደ 2 ስናልፍ የሰውን አፈጣጠር እናያለን። ዘፍ. 2፥7 እግዚአብሔር  አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ  አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ይላል። ማንን ነው ያበጀው? ሰውን። ከምን? 

ከምድር አፈር። የተበጀው ምንድር ነው? ሰው። የሕይወት እስትንፋስ እፍ ሲባልበት ምን ሆነ? ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። ሳይባልበትስ? የተበጀ ሰው ነበር እንጂ መንፈስ አልነበረም። ገና ሕያው ያልሆነ የተበጀ ሰው። በመንፈሱ ውስጥ አይደለም የሕይወት  እስትንፋስ እፍ የተባለበት። ግልጽ ነው መወሳሰብ የለበትም! ከምድር አፈር የተበጀው ሰው ነው፤ መንፈስ አይደለም። መንፈስን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር  አላለም። በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ሰውም ሕያው ነፍስ  ያለው ሆነ። እንጂ፥ መንፈስም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። አልተባለም።

  ሰው ሕያው የሆነው የሕይወት እስትንፋስ እፍ ሲባልበት ነው፤ መንፈስ እና ነፍስ  በሰው ውስጥ የሚኖሩ ነገሮች ናቸው። ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥ ሁሉንም  የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል። ኢዮ. 32፥8። ሰው ሁለንተናው፥  ሥጋው፥ ነፍሱ እና መንፈሱ ነው እንጂ ሰው መንፈስ ብቻ አይደለም። 1ተሰ. 5፥23 የሰላምም አምላክ ራሱ ሁለንተናችሁን ይቀድስ፤ መንፈሳችሁም ነፍሳችሁም  ሥጋችሁም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለ ነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ። ይላል።  

እነዚህ፥ ‘Kind ነን’ የሚሉት ሰዎች እንጀራ አባቶቻቸው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ስለሆኑ  ነው ብያለሁ። Kind ነንን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ኮሮጆ ወይም ፓኬጅ የሸመቱትም  ከእነሱ ነው። ይህ ሰው መንፈስ ነው የሚባለው ትምህርት አገራችን ውስጥ ዋልድባ  ገዳም ወይም አዋሳ አዲስ ከተፈለፈሉት ፍልፍሎች ቤት የተፈጠረ ትምህርት  አይደለም። እነዚህ አዳዲስ ፍልፍሎች ብቻ ሳይሆኑ የፍልፈል ሥራ ሠራተኞችም  ናቸው። በሥራቸው፥ በተግባራቸው ፍልፈሎች ናቸው። ፍልፈልን ገጠር ያላደጉ  አያውቁም። ፍልፈል ማለት እንደ አይጥ ወይም አይጠ መጎጥ ያለ ሆኖ መሬት ውስጥ  ጉድጓድ ቆፍሮ ውስጥ ለውስጥ እየሄደ ስራስር የሚበላ ነው። እኔ ባደግኩበት አካባቢ ገበሬዎችን በጣም የሚረብሽ ፍጡር ነው። ድንች፥ ስኳር ድንች፥ ቦዬ የሚሉት ልሌላ  ተክል ስራስር፥ በተለይ የእንሰት ስርን እንክት አድርጎ ይበላል። የእንሰት ተክል ውስጥ  መግባቱ የሚታወቀው እንሰቱ በቁሙ መድረቅ ሲጀምር ነው። አንዳንዴ በቁሙ  ይወድቃል፤ ወይም ሄደው ገፋ ሲያደርጉት እንሰቱ በቁሙ ይወድቃል። ሐሰተኛ  አስተማሪዎችም እንደ ፍልፈል ናቸው ስል ስራችንን በልተው ከላይ ያደርቁናል ማለቴ  ነው። ሲገፉን እንወድቃለን። 

የነዚህ እኛ መናፍስት ነን የሚሉ ሰዎች ትምህርት አገራችን የተወለደ ትምህርት  አይደለም ብያለሁ። አሜሪካ ውስጥ ተፈጭቶ ተቦክቶ የተጋገረ መርዝ ነው።  አንዳንዶቹ ሲኮርጁ ምኑንም ሳያስቀሩ ነው የሚኮርጁት፤ እንደ ሰነፍ ተማሪ። አንድ  ሰነፍ ተማሪ ኮርጆ ፈተናውን ሠራና ሰጠ አሉ። ወረቀት በሚመለስበት ቀን  አስተማሪዎቹ ለተማሪዎቹ ሁሉ ሰጠ። ይህ ልጅ ደግሞ ሳያፍር፥ ‘ቲቸር! የኔ የፈተና ወረቀቴ አልተሰጠኝም።’ ብሎ ሲጠይቅ፥ ‘ይሄ ያንተ ነው? አለው ውጤቱን ብቻ  አሳይቶ፤ ‘አዎ፤ ሄይ!’ ሲል፥ ‘ይሄ ስም ያንተ ነው?’ ሲለው ኩም! ለካስ፥ name  ከሚለው ቀጥሎም የራሱን ስም በመጻፍ ፈንታ የሚኮርጀውን ልጅ ስም ጽፎ ነበር።  የሐሰት ትምህርት አስተማሪዎች ሲኮርጁ ልክ እንደዚያ ናቸው። ምንም ሳያስቀሩ ነው  የሚኮርጁት። 


በ2017 አንድ መጽሐፍ ገዝቼ ነበር። መጽሐፍ ስገዛ እንደማደርገው ቆሜ በገጾቹ  እሮጥበታለሁ። ብሔራዊ ቴያትር አጠገብ የተለጠፉት ሱቆችጋ ሄጄ በኢትዮጰኝነት  ጉዳይ ላይ ስለጻፍኩና ስለምጽፍም አንዱን እንድገዛ የተነገረኝን መጽሐፍ ሳልገዛው  ማንበብ ጀመርኩ። የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ የሚል በፕሮፌሰር  ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ገና ሳነብበው ተረት ተረት ነበር የሸተተኝ።  ቢሆንም ገዛሁት። መጽሐፉ ሦስት ክፍሎች ሲኖሩት የመጀመሪያው ትንሽ ሆኖ ክፍል  ሁለትና ሦስት ሰፋፊ ናቸው። ክፍል ሁለትን እያነበብኩ የግርጌ ወይም ዋቢ ማጣቀሻዎችን ሄጄ ሳይ አማን በላይ የሚል አንድ ስም ከምንም በላይ ተደጋግሞ ተጠቅሶአል። 4 አማን በላይ ገጽ . . . አማን በላይ ገጽ . . .። 


የመጽሐፉ ክፍል አንድ ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ የኦሮሞን አበርክቶት የሚናገር ሆኖ  ጥቂት ማጣቀሻ ብቻ ያለው አጭር ክፍል ነው። በክፍል ሁለት ከ63 የግርጌ  ማስታወሻዎች አማን በላይ 31ዱን ይዞአል። ግማሽ በግማሽ ማለት ነው። በክፍል  ሦስት ደግሞ ከ56ቱ ማጣቀሻዎች 31ዱን ይዞአል። 55% ማለት ነው። የአማን በላይን መጽሐፎችም አይቼ ነበር፤ ግን፥ 'ይህስ የሚነበብ አይደለም፤ ይህ ደግሞ በእርግጥም ምንጭ የሌለው ተረት ነው፤ ይህ ጥሬ ኢትዮጰኛ ሥራ ነው' እያልኩ ተውኳቸውና  ሳልገዛ ቀረሁ። በኋላ ገዛሁት። ይህን ከላይ የጠቀስኩትን መጽሐፍ ለመጥቀስ ብቻ  ነው ያነሣሁት እንጂ ላሔስ አይደለም፤ ትዝብቴ ግን፥ ሒስም ከሆነ ሒሴ፥ የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆነ ሰው፥ ከአንድ መጽሐፍ ብቻ 50% ወይም 62 ጊዜ ከጠቀሰ፥ ያውም ምንጩ ከመደፍረሱ የተነሣ የማይታይ መጽሐፍ ከጠቀሰ ያስፈራል። ተረቶችን ዋቢ  አድርጎ እንደ ምሑራዊ ጽሑፍ ተነባቢ ካደረገ አዝማሚያችን ያስደነግጣል። የምንቀዳባቸው ምንጮች ከተበላሹ ፈሳሹ ጅረት በምንም ሂሳብ ጤና ሊሆን አይችልም። ይህ የአማራ ኦሮሞ ጉዳይ ሌላ ዘውግ ነው፤ ከብዙዎቻችን ክልል ውጪም  ነውና ይህንን ለማንሣት ወዳነሣሳኝ የእኛ ወደሆነው ልምጣ። 


ስሕተቶችን ለመንቀስ ወይም ስሕተትነታቸውን ለማሳየት ወደ ምንጩና ወደ አመንጪዎቹ መሄድ አማራጭ የሌለው የሕያሴ ሥራ ነው። ልክ አንድ ተረት የተረት አባት ሲናገረው ተረት ይመስልና፥ አንድ ምሑር በቆነጀ፥ በሰለጠነ ቋንቋ ሲናገረው  እውነት ሊመስል ይችላል። በመንፈሳዊው ረገድም ተመሳሳይ ነው። አንድ ጠንቋይ  የተናገረው ነገር የጥንቆላ ነገር መምሰል ብቻ ሳይሆን መሆኑን ለማወቅም አይከብደንም። ያንኑ ነገር ግን አንድ ሰባኪ ከመጽሐፍ ቅዱስ በወጡ ቃላት ሸቃቅጦ፥ ቀያይጦ፥ ቀባብቶ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አስመስሎ ሲያቀርብ ወይም  ቢያቀርብ በቀላሉ ልንታለልና ልንስት እንችላለን። 


አንዳንድ የስሕተት ትምህርቶችን ስንፈትሽ፥ ስናሔስ ቅርንጫፎቹን ከመመልመል  ተሻግረን ወደ ግንዱ መሄድና መግለጥ አለብን። ቅርንጫፎቹን መመርመር ፍሬያቸውን ያሳየናልና ያም ጥሩ ነው፤ መደረግ አለበት። ግን፥ ወደ ግንዱ መሄድ የአንዱን ቅርንጫፍ ብቻ ሳይሆን የቅርንጫፎቹን ሁሉ ባሕርይ እና ምንነታቸውን  ያሳየናል። ስሕተቶችን የመንቀፍና የመንቀስ ሥራ ቀላል አይደለም። ያታክታል፤  ያሳምማል፤ ያስከስሳል፤ ያስኮንናል ግን መደረግ አለበት። ስሕተቶችን የመንቀስ ሥራ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንዳልኩት ልክ ዐዛባ እንደ መዛቅ ዓይነት ነው። ያቆሽሻል፥  ያከረፋል። ግና ምን ያረጉታል? መደረግ አለበት፤ መዝዛቅ አለበት። 

ሰው መንፈስ ነው? ወይስ ሰው ነው? የሚለውን ይህንን አሳብ ስናይ፥ በእነዚህ  የስሕተት አስተማሪዎች ዘንድ እንደ አዝማች የሚደጋገም አንድ ዐረፍተ ነገር አለ፤  ያም፥ 'ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ ያድራል' የሚለው ነው።  የኮረጁት ነው። "You Are a Spirit Being; You Possess a Soul & Just Live in   a Body." (John Hamel) የሚለው ነው። Hamel ከብዙዎቹ ቃል-እምነተኞች አንዱ  ነው። በቃል-እምነት አስተማሪዎች ዘንድ ይህ፥ ‘ሰው መንፈስ ነው፥ ነፍስ አለው፥  በሥጋ ውስጥ ያድራል’ የሚለው አባባል፥ ሙሉ ተቀባይነት ያገኘ፥ የተቀዳጀ የስሕተት ትምህርት ነው። ተቀባይነት አገኘ ማለት ግን ስሕተትነቱን አይቀይረውም። ስሕተቱ  ሰውን ሰው ሳይሆን መንፈስ ማድረጉ ነው። ሰው መንፈስ ከሆነ፥ ሰው = መንፈስ ወይም ሰው እኩል ነው ከመንፈስ ጋር ማለት እንችላለን ማለት ነው። ሰው የሚለውን  ቃልም መንፈስ በሚለው ያለ ምንም ችግር መለወጥና መተካት እንችላለን ማለት  ነው። ምክንያቱም፥ a = b ካልን፥ b = a ማለት እንችላለን። የግድ a bን ባይሆንም፥ a  ከb ጋር እኩል ወይም እኩያ ነው ማለት ይቻላል።


 እነዚህ አሳች ሰዎች፥ ‘እኛ አማልክት ነን ወይም ትንንሽ አማልክት ነን’ የሚሉት በመዝ. 82፥6 እኔ ግን፦ አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤ ተብሎ ስለተጻፈ  ሳይሆን፥ ጥቅሱን እንመለከተዋለን፤ እውነተኛ ምንጩ መንፈስነታቸው፥ ማለትም  መንፈስ ነን ማለታቸው ነው። እግዚአብሔር መንፈስ፥ እኛ መንፈስ፤ ስለዚህ እኛ  እግዚአብሔር። 

ትንንሽ አማልክት ነን የሚለውን አጠራር እኛ አይደለንም የሰጠናቸው ራሳቸው ናቸው  ያሉት። Little gods with little ‘G’ የሚሉት ራሳቸው ናቸው። ይህ የኛ ፈጠራ አይደለም። እንደዚህ ያሉ ብዙ ናቸው፤ አንዱ ክሬፍሎ ዶላር የተባለው ያለውን  መስማት በቂ ነው፤ ይህንን ያለው በጉባኤው ውስጥ ነው። ከቪድዮው በቀጥታ  የወሰድኩትን ከነትርጉሙ ልጻፈው፤ 

Creflo Dollar "everything reproduces after its own kind". . . 

Dollar: "If horses get together, they produce what?" 

Congregation: "Horses!" 

Dollar: "If dogs get together, they produce what?" 

Congregation: "Dogs!" 

Dollar: "If cats get together, they produce what?" 

Congregation: "Cats!" 

Dollar: "So if the Godhead says 'Let us make man in our image', and everything  produces after its own kind, then they produce what?" 

Congregation: "gods!" 

Dollar: "gods. Little "g" gods. You're not human. Only human part of you is this flesh you're wearing."5

ትርጉም፤ እንግዲህ ሁሉም እንደየወገኑ ነው የሚወልደው፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር (ሲያመርት) እናያለን። ታዲያ እግዚአብሔር ሰው ከፈጠረና ሌሎቹ ነገሮች እንደየወገናቸው  ከወለዱ፥ ፈረሶች ሲገናኙ ምን ይወልዳሉ? ፈረሶች! ውሾች ሲገናኙ ምን ይወልዳሉ? ውሾች! ድመቶች ሲገናኙ ምን ይወልዳሉ? ድመቶች! እግዚአብሔር ደግሞ አንድ ላይ ሆኖ ሰውን እንፍጠር ሲሉ ምን እየፈጠሩ ነው? እግዜሮች! እግዜሮች እየፈጠሩ ነው። እናንተ እግዜሮች ናችሁ  ትንንሽ እግዜሮች (Little ‘G’)። እናንተ እግዜሮች ናችሁ ምክንያቱም እናንተ የመጣችሁት ከእግዚአብሔር ነው። እናንተ ሰዎች አይደላችሁም፤ ከእናንተ ሰው የሚባለው ነገር ይህ  የምትኖሩበት አካላችሁ ብቻ ነው። ብሏል። 

Little ‘G’ የሚሉትን ሌሎቹም ይሉታል። እና ይህ የኛ ቃል አይደለም፤ የራሳቸው ነው። ትንንሽ አምላኮች ነን ያስባልናቸው እኛ አይደለንም፤ እነሱ ናቸው Little ‘G’  በሉን ያሉት። ኃይሉ ዮሐንስ ትልልቅ በሉኝ ብሎ መልሶ እየቀለድኩ ነው እንደዚያ  ያልኩት ብሏል። ይቀልድም አይቀልድም፥ Little ‘G’ም እንበለው፥ ንዕሽተ አምላኽ  በለው፤ ሺማ ማጋኖ በለው፥ ወይም ጢቆ ዋቆ እንበለው፤ ልዩነት የለውም፤ ሰው ሰው  ነው፤ ኃይሉ ዮሐንስም፥ ኃይለኛው ዮሐንስም፥ ኮሳሳው ዮሐንስም፥ ሰው ነው፤ ሰው አምላክ አይደለም። ሰው አምላክ ነው ተብሎ አልተጻፈም። አራት ነጥብ። 

ኃይሉ ዮሐንስም ይህንኑ የክሬፍሎን አባባል ብሎታል፤ ‘አምላክ ምንድነው  ሚወልደው? አማልክትን ነው።’ ብሏል በአንድ ቃለ ምልልስ።
 መልሶ ስለመምሰልም  ይናገራል። በቃላት ቁማር መጫወት አንዳንዴ ሊያበላ ይችል ይሆናል፤ ግን መበላትም አለ። መምሰልና መሆን የተለያዩ ናቸው። እኔ Little ‘G’ god ነኝ ማለትና እኔ ፈጣሪዬ በአምሳሉ የፈጠረኝ አምላክ ያልሆንኩ ሰው ነኝ ማለት የተለያዩ ናቸው። Little ‘G’  godም የትኛው ‘G’ godም ማናችንም አይደለንም። ሰው ነህ፤ ሰው ነሽ፤ ሰው ነን።  እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር  ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ። 

መምሰልን ከወሰድን፥ መምሰልማ በመልኩ እንደ ምሳሌው ነው እኮ የተፈጠርነው። ሰውየው ነው ግን በመልኩ እና በምሳሌው የተፈጠረው፤ አምላክ ወይም መንፈስ  ሳይሆን። ዘፍ. 1፥26። ኃይሉ ዮሐንስ ከላይ ባልኩት ቃለ ምልልሱ መምሰል መግዛት መሆኑን ተናግሯል። መምሰል የሰማይ፥ የምድርና የባሕር ፍጥረትን መግዛት ነው  ብሏል። ግዛ የተባለው እኮ መንፈስ አይደለም፤ ወይም አምላክ አይደለም፤ ሰው ነው። ሰው እኮ ሲገዛ ኖሯል። ያውም ከመንፈስ ያልተወለደውም ጭምር! ክርስቲያን ሆነ  አልሆነ ፍጥረት ለሰው ተገዝቷል፣ ተገርቷል፤ የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና  በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል፥ ደግሞ ተገርቶአል፤ ያዕ. 1፥7።  ፍጥረት ሁሉ ለሰው ተገዝቷል፤ ከውድቀት በኋላ እንደ ልቡ ባይገዝዛለትም፥ ሲገዝዛ  ኖሯል፤ ሰውም ሲገዛ ኖሯል! እንዲያው መቀወጥ ሲያምረን እንጂ። ስንፈጠርም ሰው  እንጂ አምላክ አይደለንም። አባታችን አዳምም ሰው እንጂ አምላክ አልነበረም! ሊገዛ መፈጠሩማ በግልጽ ተጽፏል፤ ያልተጻፈውና እነዚህ አሳቾች የፈጠሩት መንፈስ  መሆኑና አምላክ መሆኑ ነው። እሱ ነው ያልተጻፈው።

እግዚአብሔር ቃላት አጥረውት አይደለም ሰውን ሰው ያለው። ሰውን ሰው ያለው  ሰው ሰው ስለሆነ ነው። የቃል-እምነት አስተማሪዎች ሰው መንፈስ መሆኑን፥ ነፍስ  ያለው እና በሥጋ ውስጥ የሚያድር መሆኑን ሲያወሳስቡ ከዚያ ለሚቀጥል ሰይጣናዊ ትምህርት ሰውን ሲያዘጋጁ ነው። ያም፥ 'ሰው በእግዚአብሔር መደብ (እነርሱ class  ይሉታል) የተፈጠረ ነው' የሚል ነው። ኃይሉ ዮሐንስም፥ ‘እኔና አብ አንድ ነን!’ ያለው  እና ሰው በሥጋ ውስጥ የሚያድር ነፍስ ያለው መንፈስ መሆኑን የተናገረው ከዚህ እኩይ ትምህርት ተንደርድሮ ነው። እነ ቤኒ ሂን፥ ኮፕላንድ፥ ሄግን፥ ሮበርትስ፥  ሌሎችም ቀድመውት ብለውታልና ይህ እርሱ ያስተጋባው እርሱ የፈጠረው አዲስ  ትምህርት አይደለም። ‘የነሱን ትምህርት አላስተምርም፤ የነሱን ወስጄ የራሴን ነው  የማስተምረው’ ብሏል። መስሎት፤ ወይም ሊያታልል። ሱቁን ነው የቀየረው እንጂ ሸቀጡን አልቀየረም። ከነዚያ፥ Man is a spirit being, has a soul, lives in a  bodyን ሰማ፤ በእንግሊዝኛ። ከዚያ፥ ሰው መንፈስ ነው፤ ነፍስ አለው፤ በሥጋ ውስጥ  ያድራል አለ፤ በአማርኛ። ይህ ነው የራሴ የሚለው። እኔና አብ አንድ ነን ማለትን  እየጨመረበት።

አንዴ በኤልሻዳይ ቲቪ ከመጋቢ ተሾመ ዳምጠው ጋር ቀርቦ፥ ‘እኔና አብ አንድ ነን  አላልኩም፤ ማለቴ ትዝ አይለኝም።’ ብሎ ብዙ ሳይቆይ እኔና አብ አንድ ነን አለ።  ባዕድ-ቅይጡ ወንጌል ለተሰኘው ዘጋቢ ቪድዮ ምላሽ ሲሰጥም ያንኑ ደገመው።  መድገም ብቻ አይደለም እንዲያውም የክርስቲያን አገልጋይ ትክክለኛነት መለኪያ  አደረገው። ከአንድ አገልጋይ ነኝ ከሚል ሰው ጋር ቁጭ ብሎ ለማውራት ሲጀመር  መስፈርት ያደረገው ምን እንደሆነ ሲናገር፥ ያ ሰው፥ ‘ስለ ሰው ምን እንደሚያስብ  እጠይቀዋለሁ፤ እኔና አብ አንድ ነን የማይል ከሆነ መንፈሳዊ ነገር ስላልገባው  መንፈሳዊ ነገር ከዚያ ሰው ጋር አላወራም፤ ስለ ፖለቲካ ስለ ሌላ ነገር ብቻ አውርቼ  እለያያለሁ፤’ አለ።

ይህ ሰው፥ ‘እኔና አብ አንድ ነን!’ ካለ፥ ቀጥሎ፥ ‘እኔን ያየ አብን አየ’ ማለት ምን  ይከለክለዋል? ምንም። ሰውን ወደ እግዚአብሔር መደብ ለማስጠጋት ሰውን ሰው ነው  ከማለት ይልቅ መንፈስ ነው ማለት የሚቀለው ለዚህ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር  መንፈስ ነውና ሰውም መንፈስ ነው ከተባለ በኋላ፥ ‘ሰው እግዚአብሔር ነው’ ወይም፥ ‘የእግዚአብሔር ዓይነት ነው’ ማለት ከባድና ሩቅ አይሆንም። እኔና አብ አንድ ነን ማለት እኮ፥ እኔን ያየ አብን አይቷል ማለት እኮ ሌላ ምንም አይደለም፤ እኔ ክርስቶስ  ነኝ ማለት ነው። ‘እኔ ክርስቶስ ነኝ’ እያሉ በስሙ የሚመጡ መኖራቸው ደግሞ ቀድሞ ተነግሮናል። 

‘እኔና አብ አንድ ነን’ ያለ ከኢየሱስ በቀር ሌላ የለም። ይህን ያለው ደግሞ የሆነው እርሱ ነው። ይህ እውነት ከጳውሎስና ከጴጥሮስና ከዮሐንስ ይህ ተሰወረና፥ ለ2ሺህ ዓመታት ተደብቆ ቆየና እሱና አብ አንድ መሆናቸው አሁን ለኃይሉ ዮሐንስ ተገለጠ?  እንደዚህ ያለውን ‘እኔና አብ አንድ ነን’ እግዚአብሔርን መስደብ በእግሩ ስር ተቀምጦ የተማረበት አሳዳጊው ኮፕላንድም አልተናገረም። እንዲህ ያለውን፥ ስድብ አያቱ  ሄግንም ‘I and the Father are one!’ ብሎ አልተናገረም። 


በዮሐ. 10፥30 ጌታ፥ ‘እኔና አብ አንድ ነን’ ባለ ጊዜ ምን ነበር የሆነው? በቁ. 31 እንደተጻፈው አይሁድ ሊወግሩት ደግመው ድንጋይ አነሡ። ነው የተባለው። ለምን? እኔና አብ አንድ ነን ማለት እኔ ያህዌ ነኝ ማለቱ ነው። ምን ማለቱ መሆኑን አሳምረው  አውቀውታል። ገብቷቸዋል። እኔና አብ አንድ ነን ሲል፥ በነሱ ግምት ተሳድቧል።  እርሱ ግን አምላክ ነው፤ በሥጋ የመጣ እግዚአብሔር ነው። ሥጋ የሆነ ቃል ነው።  በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረ ነው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር የነበረ ነው። ዓለማትንና እነዚህን ተሳድበሃል የሚሉትንም የፈጠረው እርሱ ነው። እኔና አብ አንድ ነን ሲል ለነሱ መሳደብ ነው እርሱ ግን ይህንን ያለውን ነው።

ኢየሱስ ታላቅ ወንድምህ አይደለም፤ እርሱ ጌታህ ነው። እሱ ወንድሞቼ ያለው እንዳላፈረብህ ያሳያል እንጂ አንተ እንድትመጻደቅ አያደርግህም። ወንድሞቼ ያለው በሥጋና ደም ተካፍሎ እኛን የእግዚአብሔር ልጆች ማድረጉንና በትንሣኤም ብኵርናውን ያሳያል እንጂ ከሐዋርያቱና ከደቀ መዛሙርቱ አንዳቸውም፥ ‘ታላቅ ወንድማችን’ እያሉ አልገለጡትም። ይህ ግልጽ እውነት ነው። ማናቸውም ይህንን አላሉም። በሥጋ ግማሽ ወንድሞቹ የነበሩት ያዕቆብና ይሁዳ እንኳ፥ ‘የጌታ ታናሽ ወንድም’ እያሉ ሳይሆን፥ ‘የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ’ እያሉ ነው የጻፉት፤ ሁለቱንም  መልእክቶች ተመልከቱ። ያዕቆብ በመግቢያ ቃሉ፥ የእግዚአብሔርና የጌታ የኢየሱስ  ክርስቶስ ባሪያ ያዕቆብ ለተበተኑ ለአሥራ ሁለቱ ወገኖች፤ ሰላም ለእናንተ ይሁን። አለ፤  ያዕ. 1፥1። ይሁዳም፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ተወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ፤ አለ፤ ይሁ. 1። እነሱ ባሪያ ከሆኑ እርሱ ጌታ ነው። 

ጌታ ማለት ልጅነትህን አይፍቀውም። ‘ታላቅ ወንድሜ’ ማለት ግን ባርነትን እንዲፍቀው ሆን ብለው የቀመሯት ቀመር ናት! በእውነቱ፥ የቃለ እምነት አሳቾች፥  ‘ባሪያ’ የምትለዋን ቃል አይወዷትም። ታላቅ ወንድምህ ከሆነ አቻህ ነው፤ አቻው ነህ፤  ሽርክህ ነው፤ አብረኸው ማኪያቶ ትጠጣለህ፤ አዛዥህ አይደለም፤ ታላቅህ ቢሆንም ባትታዘዘውም ምንም አይደለም፤ ወይም መርጠህ ከታዘዝከው ልታስረዳውና  ልታሳምነው ትችላለህ። ታላቅ ወንድምህ፤ ግን ንቀት ነው! ስድብ!

ጌታ፥ ‘እኔና አብ አንድ ነን’ ሲል፥ በአይሁድ ግምት ተሳድቧል። እርሱ ግን አምላክ ስለሆነ፥ እግዚአብሔር ስለሆነ፥ በሥጋ የመጣ ቃል ስለሆነ አልተሳደበም። እርሱና አብ  አንድ ናቸዋ! ዛሬ ግን ሌሎች ተሳዳቢዎች በቅለውልናል። በመጀመሪያ ከእግዚአብሔር  ጋር ያልነበሩ፥ እግዚአብሔር ያልነበሩ፥ በሥጋ የተገለጠ አምላክ ያልሆኑ፥ እኔና አብ  አንድ ነን ይሉናል። ኃይሉ ዮሐንስን ተሳድበሃል የሚለው እስካሁን የጠፋ አይመስለኝም፤ አልሰማም እንጂ ከዚህ በፊት ጥቂት ወገኖች ነግረውታል፤ በስሕተቶቹ  ላይም ጽፈዋል። አልሰማም እንጂ። እኔም ልበለው፤ ኃይሉ ዮሐንስ እና ይህን መሰል ስድብ በእግዚአብሔር ላይ የምትናገሩ፥ ተሳድባችኋል፤ አንተና አብ አንድ  አይደላችሁም። ሌሎችም ካላችሁ፥ እናንተና አብ አንድ አይደላችሁም። እናንተን  ማየት አብን ማየት አይደለም። ስድባችሁን አርቁልን። 

እነዚህ ከላይ ያየናቸው ሁለቱ ትልልቅ አደጋዎች ናቸው። 1ኛው አደጋ፥ ሰው መንፈስ ከሆነ ሥጋው በኃጢአት ቢረክስም መንፈሱ የታተመችና የተጠበቀች ናት የሚል የኃጢአት ፈቃጅነት፥ አለማማጅነትና ተለማማጅነት ሲሆን፥ 2ኛው አደጋ፥ ሰው አምላክ ነው ማሰኘቱ ነው።

ኮራጆች



JESUS IS RISEN! 
 SUBSCRIBE
 talewgualu video
 https://www.youtube.com/watch?v=ANJk-wzRU_Q

Comments