የተጽዕኖ አሻራ ያላቸው ሰዎች ከጀርባችን አሉ!
ብዙዎች የማያስተውሉት በምድር ላይ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በመልካም ደግሞም በክፉ የተጽዕኖ አሻራ ያላቸው ሰዎች ከጀርባቸው መኖራቸውን ነው፡፡
ወዳጆች ዛሬ በእኔ ሕይወት በተለያየ አቅጣጫ ከእኔ ጀርባ በተለያ መንገድ የተጽዕኖ አሻራ ባላቸው ሰዎች አማካኝነት እግዚአብሔርን ማመስገን ፈለኩ፡፡
ከሁሉ አስቀድሜ አፍቃሪ አባቴን በኢየሱስ ክርስቶስ የመቤዠት ሥራ ነፃ ስላወጣኝ፣ ሕይወትን ሰጥቶ አዲስ ፍጥረት፣ ጻድቅ፣ ቅዱስ እና ልጁ በማድረግ በክርስቶስ ውስጥ በቀኙ ስላስቀመጠኝ አመሰግነዋለሁ።
በወላጆቼ አማካይነት ወደዚህ ምድር ከመጣው በኋላ በመንፈሳዊ ረገድ ባይሆንም እንኳ የመጀመሪው የተጽዕኖ አሻራ ያላቸው ወላጅ እናቴ (እትይቱ) እና እኔ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ስሆን የአንድ ዓመት ልጅ ሆኜ አባቴን በሞት ካጣሁበት ጊዜ ጀምሮ ልክ እንደ አባት ሆኖ ያሳደገኝ የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ወንድሜ ናቸው፡፡ በአሁን ወቅት ሁለታችሁም ከዚህ ምድር ተለይታችሁ በክርስቶስ ካዳናችሁ አባታችሁ ጋር ብትሆኑም እናንተ መቼም ቢሆን በልቤ ትልቅ ሥፍራ አላችሁ፣ ስለእናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡
በ1980ቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገዳመ ኢየሱስ ሰንበት ትምህርት ቤት አመራር ላይ የነበራችሁ ወንድሞች እና እህቶች ከእናንተ ጋር በተለያዩ አባቶችና ወንድሞች የወንጌልን እውነት በማወቄና ለሌሎች ወንጌልን በማድረስ ቅናት በተለያዩ መንገዶች አብሬአችሁ ማገልገል በመቻሌ ስለእናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
የአዲስ ክርስቲያን ሴንተር ቤተክርስቲያን መሪ መጋቢ መስፍን ገ/እግዚአብሔር እና በተለያዩ ጊዜያት በቤተክርስቲያኒቱ የነበራችሁና ያላችሁ አብሬአችሁ የማገልገል ዕድልን ያገኘሁባችሁ፣ ደግሞም በቤተክርስቲያኒቱ የጸጋ ወንጌል መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አማካኝነት ከሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የተዋወኳችሁ ወንድሞች እና እህቶች ስለእናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
ኪያዬ የኔ ውድ በሕይወቴ አንቺን የመሰለ ድንቅ ስጦታ በማግኘቴ፣ ደግሞም ተወዳጅ የሆኑ ወላጆችሽ በዚህ ምድር ለመገኘትሽ ምክንያት በመሆናቸው ስለእናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
በመጨረሻም በእኔ ላይ በተለያዩ መንገዶች የክፉ ተጽዕኖ ያመጣችሁ ሰዎች እግዚአብሔር ለእኔ ማን እንደሆነ እና እኔ በእግዚአብሔር ዘንድ ማን እንደሆንኩኝ እንዳስተውል አድርጋችሁኛልና ስለእናንተ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡
Comments