የኢየሱስ ደም ለሁሉም ነገር ብቻውን በቂ ነው!
ደሙ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ያህል በእኛም ልብ ውስጥ ስፍራ ሊኖረው ይገባል። ዋች ማኒ ሲናገር "የልጁን ደም ታላቅ ዋጋ በትክክል ለማወቅ አባት ስለ ልጁ ደም ያለውን ዋጋ ማወቅ አለብን" አለ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ኃጢአተኛውን ለማዳን ከክርስቶስ ደም በስተቀር ሌላ መንገድም ሆነ ሐሳብ የለውም።
በሰውነታችን ውስጥ ያለው ደም በሙሉ ቢፈስ የሚቀረው በድናችን ብቻ ነው። ልክ እንደዚሁ መሃከላዊውን ነጥብ ማለትም የክርስቶስን መስዋዕታዊ ሞት የሚያሳየውን የደም መፍሰስ (የመስቀል ሥራ) ብንዘለው በቤተክርስቲያን ጥቅመ ቢስ ሥርዓት ብቻ ይኖራል።
በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደሙ ከፍ ያለ ስፍራ እንዳለው ስንመለከት እግዚአብሔር ምን ዓይነት ትምህርት መመማር እንዳለብን እንደፈለገ መገንዘብ ከባድ አይሆንም።
ሰዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ውስጥ ያለውን ከፍተኛ መንፈሳዊ እሴት እንዲመለከቱ ለማድረግ የመንፈስ ቅዱስን ብርሃን ይጠይቃል።
በኢየሱስ ደም ያገኘናቸውን የተለያዩ በረከቶች ስናስብ "መዋጀት" የሚለው ቃል ሁሉንም ያጠቃልላቸዋል፡፡
"ለራሳችሁና መንፈስ ቅዱስ ኤጲስቆጶሳት አድርጎ በላዩ ለሾማችሁ መንጋ ሁሉ ተጠንቀቁ፤ በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ጠብቁ።" (ሐዋርያት ሥራ 20:28 NAS)
"ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት የተዋጃችሁት በሚጠፋ ነገር፣ በብር ወይም በወርቅ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፤ ነገር ግን እናንተ የተዋጃችሁት ነውርና እንከን እንደሌለበት በግ ደም፣ በክርስቶስ ክቡር ደም ነው።" (1 ጴጥሮስ 1:18-19 NASV)
ስለኢየሱስ ደም ስንናገር ዘላለማዊ እና ፍጹም የሆነውን የመቤዠቱን ሥራ በተመለከተ እየተናገርን ነው።
1. በደሙ የኃጢአት ይቅርታ እና እርቅ አግኝተናል፡-
"በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን፤" (ኤፌሶን 1:7 NASV)
"እርሱ ከጨለማ አገዛዝ ታደገን፤ ወደሚወደው ልጁ መንግሥትም አሻገረን፤ በእርሱም መዋጀትን በደሙ አግኝተናል፤ ይህም የኀጢአት ይቅርታ ነው።" (ቈላስይስ 1:13-14 NASV)
"እናንተም በበደላችሁና የሥጋችሁን ኀጢአታዊ ባሕርይ ባለ መገረዝ ሙታን ሳላችሁ፣ እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረጋችሁ ፤ ኀጢአታችንንም ሁሉ ይቅር አለን፤" (ቈላስይስ 2:13 NASV)
ጳውሎስ በመልእክቶቹ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም (የመስቀሉ ሥራ) የፈጸመውን በደልን የመፋቅ የመደምሰስ ችሎታ በተደጋጋሚ ጽፏል፡፡
መጥምቁ ኢየሱስን ሲያስተዋውቅ በዮሐንስ 1፡29 ላይ "እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" አለ፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ምን ያህል የተለየ እንደሆነ እንደገና ልብ እንበል፡፡
የኃጢአት ይቅርታ እንዲሆን ደም መፍሰስ አለበት፡፡ ኢየሱስ ያለውን ስሙ በሉቃስ ምዕራፍ 22 ቁጥር 20 ላይ "ለብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው" አለ፡፡
ጽዋውን ስንካፈል ይቅር እንደተባልን እና እንደጸደቅን አውቀን መሆን አለብን፡፡
ሰው በእግዚአብሔር ፊት በኃጢአት እዳ ተጠያቂ ነው፡፡ ተጠያቂነት ደግሞ እዳ ነው፡፡ እዳ ምን እንደሆነ እናውቃለን? እዳ ማለት አንድ ሰው ከሌላው ሰው የሚፈልገው ነገር ማለት ነው፡፡
የስርየት መሰረታዊ ትርጉሙ በደልን ማስወገድ ነው፡፡
"በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤" (ሮሜ 3:24-25 NASV)
"ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኀጢአታችን ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው።" (1 ዮሐንስ 4:10 NASV)
የግሪኩ ቃል አፌሲስ ዋነኛ ትርጉሙ ከሚያስር ነገር፤ ከሰንሰለት መፍታት (ሉቃስ 4፡18) ወይም ከሚያስጨንቅ እዳ ወይም ግብር (አስቴር 2፡18) ነጻ ማውጣት ነው፡፡
የስርየት ቀን ማለት ሌላው ያንተን ስፍራ ወሰደ፣ ያንተን ዕዳ ከፈለ ወይም ለአንተ ሲል ህይወቱን ሰጠ፣ ይቅር አለህ ማለት ነው። በብሉይ ኪዳን ለአንድ ዓመት ሲሆን በአዲስ ኪዳን ግን አንዴ ለዘላለም ነው፡፡
"ነገር ግን እነዚህ መሥዋዕቶች በየዓመቱ ኀጢአትን የሚያስታውሱ ናቸው፤ ምክንያቱም የኮርማዎችና የፍየሎች ደም ኀጢአትን ማስወገድ አይችልም።" (ዕብራውያን 10:3-4 NASV)
"እንዲህ ቢሆን ኖሮ፣ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ክርስቶስ ብዙ ጊዜ መከራን መቀበል ባስፈለገው ነበር። አሁን ግን በዘመናት መጨረሻ ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ኀጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል።" (ዕብራውያን 9:26 NASV)
2. በደሙ መለኮታዊ ጥበቃ አግኝተናል፡-
"ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን አልፋለሁ፤ ግብፅን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም።" (ዘፀአት 12:13 NASV)
በመጀመሪያው የፋሲካ በዓል ወቅት በጉን አርደው ደሙን በበራቸው መቃን እና ጎበን ላይ አደረጉ፡፡ ይህ ደግሞ አጥፊው ቤተሰቦቻቸውን እንዲያልፍ አደረገው፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር "ደሙን ባየሁ ጊዜ አልፋለሁ" ብሏልና፡፡
የጥላው በግ ደም እንደዚህ ያሉትን ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ውጤቶችን ማምጣት ከቻለ የእውነተኛው በግ ደም የኢየሱስ ደም እንዴት የበለጠን ነገር አያደርግም፡፡
3. በደሙ ጸድቀናል፡-
"አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በእርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቊጣ እንዴት አንድንም!" (ሮሜ 5:9 NASV)
የእግዚአብሔር ልጅ የኃጢአትን ቅጣት በክቡር ደሙ ከፍሏል፡፡ ስለዚህ ከጽዋው ስንካፈል ይቅር እንደተባልን እና እንደጸደቅን እንወቅ፡፡
መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን ሲያስተዋውቅ በዮሐንስ 1፡29 ላይ "እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" አለ፡፡ ይህ ከብሉይ ኪዳን ምን ያህል የተለየ እንደሆነ እንደገና ልብ እንበል፡፡ ኢየሱስ ኃጢአትን አስወግዷል፡፡ በዚህ ምክንያት ከዚህ በኋላ ለኃጢአት ሌላ መሥዋዕት አይኖርም ማለት ነው።
"ጽድቅ" የሚለው ቃል በአዲስ ኪዳን ግሪክ "ዲካይሱኔ" የሚባል ሲሆን ቃሉ "ዲኬ" ከሚለው ስርወ-ቃል (Root Word) የመጣ ነው።
"ዲኬ" ማለት "ትክክል" (Right) ማለት ነው። እንዲሁም በዕብራይስጥ "ጸዴቅ" የሚል ሲሆን ትርጉሙ "ትክክል፣ ንጹሕ" ማለት ነው። እንግዲህ በቃሉ ትርጉም መሰረት አንድ ሰው ጸደቀ ማለት "ትክክል" ወይም "በደል-የለሽ" ሆነ ማለት ነው።
4. በደሙ መንጻት እና መቀደስ ሆኖልናል፡-
"ነገር ግን እርሱ በብርሃን እንዳለ፣ እኛም በብርሃን ብንመላለስ እርስ በእርሳችን ኅብረት አለን፤ የልጁም የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻናል።" (1 ዮሐንስ 1:7 NASV)
"እንዲሁም ኢየሱስ በራሱ ደም አማካይነት ሕዝቡን ሊቀድስ ከከተማው በር ውጭ መከራን ተቀበለ።" (ዕብራውያን 13:12 NASV)
ከኃጢአት መንጻት ማለት ከህሊና ክስ መዳን ብቻ ሳይሆን ከኃጢአትም ብክለት መዳን ማለት ነው፡፡
"የውጭ አካላቸው ይነጻ ዘንድ በረከሱ ሰዎች ላይ የሚረጨው የፍየሎችና የኮርማዎች ደም እንዲሁም የፍየሎችና የጊደር ዐመድ የሚቀድሳቸው ከሆነ፣ በዘላለም መንፈስ አማካይነት ራሱን ነውር አልባ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው የክርስቶስ ደም ሕያው እግዚአብሔርን እንድናመልክ ኅሊናችንን ከምውት ሥራ እንዴት ይበልጥ ያነጻ ይሆን!" (ዕብራውያን 9:13-14 NASV)
"ፍጹም ሊያደርጋቸው ቢችል ኖሮ፣ መሥዋዕት ማቅረቡን ይተዉት አልነበረምን? ደግሞም ለአምልኮ የሚቀርቡት ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስለሚነጹ፣ በኅሊናቸው ኀጢአተኝነት ባልተሰማቸውም ነበር።" (ዕብራውያን 10:2 NASV)
"ከክፉ ኅሊና ለመንጻት ልባችንን ተረጭተን፣ ሰውነታችንንም በንጹሕ ውሃ ታጥበን፣ በእውነተኛ ልብና በሙሉ እምነት ወደ እግዚአብሔር እንቅረብ።" (ዕብራውያን 10:22 NASV)
ቅድስና ማለት ከእግዚአብሔር ጋር አንድ መሆን ማለት ነው፡፡
ቅድስና በውስጣችን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ከመሆን የተለየ ነገር አይደለም፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝብ ቅድስና ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት ውጤት ነው፡፡
ኢየሱስ ራሱን የቀደሰው በመከራውና በሞቱ ነው፡፡ ለእኛም ደግሞ መከራን ከተቀበለ በኋላ የቅድስና ምክንያት ሆኖልናል፡፡
"እነርሱ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ፣ ራሴን ስለ እነርሱ ቀድሻለሁ።" (ዮሐንስ 17:19 NASV)
"ሁሉ ነገር ለእርሱና በእርሱ የሚኖር እግዚአብሔር፣ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ለማምጣት፣ የድነታቸውን መሥራች በመከራ ፍጹም ሊያደርገው የተገባ ነበር። ሰዎችን የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሰዎች ከአንድ ቤተ ሰብ ናቸው፤ ስለዚህ ኢየሱስ ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው ዐያፍርም፤" (ዕብራውያን 2:10-11 NASV)
ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማድረጉ የዘላለም መፍትሔ ተገኘ፡፡
"ቀጥሎም፣ እነሆኝ፤ ፈቃድህን ለማድረግ መጥቻለሁ አለ፤ ሁለተኛውን ለመመሥረት የመጀመሪያውን ሻረ። በዚህ ፈቃድ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ አማካይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቀረበው መሥዋዕት ተቀድሰናል።" (ዕብራውያን 10:9-10 NASV)
5. በደሙ ቀርበናል፡-
"አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።" (ኤፌሶን 2:13 NASV)
መጋረጃው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ሆኖ ሰው እንዳይጠፋ ይከላከላል። መስቀል ላይ እስኪቀደድ ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት አይቻልም።
"ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊ፣ ከቀይ ማግና በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃ አብጅ፤ እጀ ብልህ ሠራተኛም ኪሩቤልን ይጥለፍበት።" (ዘፀአት 26:31 NASV)
"ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ። በዚያን ጊዜ የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ፤ ምድር ተናወጠች፤ ዐለቶችም ተሰነጣጠቁ፤" (ማቴዎስ 27:50-51 NASV)
በአዲሱ ኪዳን መካከለኛ እና ፍፁምነታችን በሆነው በኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብተናል። በኢየሱስ ደም ወደ እግዚአብሔር መገኘት ለመግባት እና ለመቆየት ድፍረት አለን።
"እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ በኢየሱስ ደም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ለመግባት ድፍረት አግኝተናል፤ ይኸውም በመጋረጃው ማለት በሥጋው በኩል በከፈተልን አዲስና ሕያው መንገድ ነው።" (ዕብራውያን 10:19-20 NASV)
የኢየሱስ ደም በድፍረት ወደ እግዚአብሔር በመምጣት በፊቱ በትክክል መቆም አድርጎናል፡፡ እናም ስንጸልይ እርሱ እንደሚሰማን እርግጠኛ መሆን እንችላለን፡፡
6. ድል በደሙ አግኝተናል፡-
"እነርሱም በበጉ ደም፣ በምስክርነታቸውም ቃል፣ ድል ነሡት፤ እስከ ሞት ድረስ እንኳ፣ ለነፍሳቸው አልሳሱም።" (ራእይ 12:11 NASV)
ሰይጣን በብሉይ ዘመን ኢዮብን እና ካህኑ ኢያሱን የመክሰስ መብት አግኝቶ ነበር፡፡
"በሌላ ቀን ደግሞ፤ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ። ሰይጣንም ከእነርሱ ጋር በእግዚአብሔር ፊት ሊቆም መጣ። እግዚአብሔር ሰይጣንን፣ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፣ በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም፤ ያለ ምክንያት እንዳጠፋው ብትወተውተኝም፣ ይኸው ፍጹምነቱን እንደ ጠበቀ ነው አለው። ሰይጣንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ ቍርበት ስለ ቍርበት ነው እንዲሉ ሰው ለሕይወቱ ሲል ያለውን ሁሉ ይሰጣል፤ እስቲ እጅህን ዘርግተህ ዐጥንቱንና ሥጋውን ዳስ፤ በእርግጥ ፊት ለፊት ይሰድብሃል።" (ኢዮብ 2:1-5 NASV)
"እርሱም ሊቀ ካህኑን ኢያሱን በእግዚአብሔር መልአክ ፊት ቆሞ፣ ሰይጣንም ሊከሰው በስተ ቀኙ ቆሞ አሳየኝ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አንተ ሰይጣን፤ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ኢየሩሳሌምን የመረጠ እግዚአብሔር ይገሥጽህ፤ ይህ ሰው ከእሳት የተነጠቀ ትንታግ አይደለምን?” አለው። ኢያሱም ያደፈ ልብስ ለብሶ በመልአኩ ፊት ቆሞ ነበር።" (ዘካርያስ 3:1-3 NASV)
ዲያብሎስን በሞት ላይ ሥልጣን ነበረው፡፡ ክርስቶስ በሥጋ የመጣው እርሱን ለመሻር ነው፡፡
"ልጆቹ በሥጋና በደም እንደሚካፈሉ እርሱ ራሱ ደግሞ ያንኑ ተካፈለ፤ ይኸውም በሞት ላይ ኀይል ያለውን ዲያቢሎስን በሞቱ ኀይል እንዲደመስስ ነው፤ እንዲሁም በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሞት ፍርሀት ባርነት የታሰሩትን ነጻ እንዲያወጣ ነው።" (ዕብራውያን 2:14-15 NASV)
ዲያቢሎስ እኛን መክሰስ አይችልም፡፡ ለምን? ክርስቶስ ለክስ ምክንያት የሆነው ሕግ የሚጠይቀውን ጽድቅ በሙሉ አሟልቶ በመስቀል አስወግዶታል፡፡
"ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው። የአለቆችንና የባለ ሥልጣናትንም ማዕረግ በመግፈፍ በመስቀሉ ድል ነሥቶ በአደባባይ እያዞራቸው እንዲታዩ አደረገ።" (ቈላስይስ 2:14-15 NASV)
ክርስቶስ ከሞት ሲነሣ አለቆችንና ስልጣናትን ትጥቅ አስፈታቸው፡፡ ማለት ስልጣናቸውንና ኃይላቸውን በመግፈፍ (በማጥፋት፣ ሽባ በማድረግ) ምርኮኞች መሆናቸውን በአደባባይ በይፋ እንዲታዩ በማድረግ አደረጋቸው፡፡ በሌላ አነጋገር አዋረዳቸው ማለት ነው፡፡
ጆን ማክአርተር ሲገልጽ፡- ሰይጣን መሳሪያውን አጥቷል፡፡ ገዢዎች እና ባለ ሥልጣናት (የወደቁ መላእክቶች) በእርሱ [በክርስቶስ] ድል መደረጋቸው በአደባባይ ተገልጠዋል፡፡ እዚህ ላይ ያለው ሥዕል እንደ ድል አድራጊው የሮማ ጄኔራል ዓይነት ነው፡፡ ድል ያደረጉትን ምርኮኞች በሮማውያን ጎዳናዎች ላይ እንደሚያዞራቸው ነው፡፡
አሁን ጉዳዩ/ ፋይሉ ስለተዘጋ በህይወት ከክርስቶስ ጋር አንድ በመሆናችን ብቻ ምንም በማንኛውም ጊዜ በሚገጥመን ውድቀት ዲያቢሎስ ሕግን ተጠቅሞ ሊኮንነን አይችልም፡፡
"ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤" (ሮሜ 8:1 NASV)
ዘ ፓሽን የሚባለው ትርጉም "ስለዚህ አሁን ጉዳ ተዘግቷል፡፡ ከተቀባው ከኢየሱስ ጋር በሕይወት አንድነት በሚቀላቀሉት ላይ ምንም ዓይነት የክስ ድምፅ አይኖርም" ይላል።
ኢየሱስ ሕጉ የሚጠይቀውን ፅድቅ በሙሉ ያሟላ ስለሆነ በማንኛውም ጊዜ በሚገጥመን ውድቀት ዲያቢሎስ ሕግን ተጠቅሞ ሊኮንነን አይችልም፡፡ ምክንያቱም የኢየሱስ መስዋዕት ያለፈውን (past tense) የአሁኑንና (present tense) የወደፊቱን (future) ጊዜ ያማከለ ነውና፡፡
ዲያቢሎስ የትላንት ውድቀታችንን በማሣየት ሕግን ተጠቅሞ ሊኮንነን ሲፈልግ በሮሜ 5:17 እና በ2ኛ ቆሮንቶስ 5:21 ላይ እንደተፃፈው በታላቅ ድምፅ ፅድቅ ስጦታ መሆኑን እንንገረው እኔ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ፅድቅ ነኝ እንበለው፡፡
በራእይ 1:4-6 ላይ በደሙ ያገኘነው መብት በክህነት ለማገልገል ብቻ ሳይሆን በንጉሣዊ ኃይል ለመግዛትም ነው፡፡
በ2ኛ ቆሮንቶስ 2:14 ላይ እንደተፃፈው አሁን በሥፍራ ሁሉ የምሥራቹን ይዘን የምንዞረው ለድል ሳይሆን ከድል ነው፡፡
Vist http://skillsharevideoblog.blogspot.com
Comments