እውነተኛው ወንጌል!
ከአይሁድ እምነት ወደ ክርስትና የመጡ ሐሰተኛ ወንድሞች ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ብለው ነበር፡፡ ስለዚህም የሰበከው ወንጌል እውነተኛ ወንጌል አይደለም ብለዋል። የገላትያ መልእክቱ የመጀመሪያ ጥቅስ ለሐዋርያነቱ መሟገቻ እንደሆነ ሁሉ የሰበከውም የወንጌል እውነተኛና ብቸኛው እውነተኛ ወንጌል ነው። ይህንም ከዚህ በታች ባሉት ንግግሮቹ መረዳት እንችላለን፡፡
"በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ" (ገላትያ 1፡1)
"በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ ወደ ልዩ ወንጌል እንዲህ ፈጥናችሁ እንዴት እንዳለፋችሁ እደነቃለሁ፤ እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። አስቀድመን እንዳልን እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን። ሰውን ወይስ እግዚአብሔርን አሁን እሺ አሰኛለሁን? ወይም ሰውን ደስ ላሰኝ እፈልጋለሁን? አሁን ሰውን ደስ ባሰኝ የክርስቶስ ባሪያ ባልሆንሁም። ወንድሞች ሆይ፥ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም አልተማርሁትምም። በአይሁድ ሥርዓት በፊት እንዴት እንደ ኖርሁ ሰምታችኋልና፤ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ያለ ልክ አሳድድና አጠፋ ነበር፥ ለአባቶችም ወግ ከመጠን ይልቅ እየቀናሁ በወገኔ ዘንድ በዘመኔ ካሉት ብዙዎችን በአይሁድ ሥርዓት እበልጥ ነበር።" (ገላትያ 1፡6-14)
ይህም ማለት ጳውሎስ ፈሪሳዊ በሆነ ጊዜ በዘመኑ ከወገኖቹ ከብዙዎቹ ይቀድማል፡፡ ከሌሎቹም ይልቅ ለአባቶች ወግ እጅግ የሚቀናና የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን በማሳደድ ከእነርሱ እጅግ አልፎ ነበር።
ሐሰተኛ ወንድሞች ጳውሎስ ወንጌሉን ከሰው እንጂ እንደ እውነተኛ ሐዋርያ ከጌታ አልተቀበለውም ይሉ ነበር፡፡ ለዚህ ሀሳብ የጳውሎስ ምላሾች በአምስት እውነታዎች ተገልጸዋል፡፡
ሀ. የመጀመሪያው እውነታ!
"ነገር ግን በእናቴ ማኅፀን ሳለሁ የለየኝ በጸጋውም የጠራኝ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስለ እርሱ ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ልጁን በእኔ ሁኔታ ሊገልጥ በወደደ ጊዜ፥ ወዲያው ከሥጋና ከደም ጋር አልተማከርሁም፥ ከእኔም በፊት ሐዋርያት ወደ ነበሩት ወደ ኢየሩሳሌም አልወጣሁም፥ ነገር ግን ወደ ዓረብ አገር ሄድሁ እንደ ገናም ወደ ደማስቆ ተመለስሁ።" (ገላትያ 1፡15-17)
ለ. ሁለተኛው እውነታ!
"ከዚህ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም ወጥቼ ከእርሱ ጋር አሥራ አምስት ቀን ሰነበትሁ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላየሁም። ስለምፅፍላችሁም ነገር፥ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ሐሰት አልናገርም።" (ገላትያ 1፡18-20)
ሐ. ሦስተኛው እውነታ!
"ከዚያ ወዲያ ወደ ሶርያና ወደ ኪልቅያ አገር መጣሁ። በክርስቶስም ያሉት የይሁዳ ማኅበሮች ፊቴን አያውቁም ነበር፤ ነገር ግን፦ ቀድሞ እኛን ያሳድድ የነበረ፥ እርሱ በፊት ያጠፋው የነበረውን ሃይማኖት አሁን ይሰብካል ተብሎ ሲነገር ይሰሙ ነበር፤ ስለ እኔም እግዚአብሔርን ያከብሩ ነበር።" (ገላትያ 1፡21-24)
መ. አራተኛው እውነታ!
"ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤ ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም። አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤" (ገላትያ 2፡1-9)
በዚህ ጥቅስ ውስጥ ብዙ እውነታዎች አሉ፡፡
1. የሰበከውን ወንጌል ነገራቸው።
2. ይህንም ያደረገው ለሐዋርያት ምንም ነገር ለማስተማር አይደለም፡፡
3. ቲቶንም ከእርሱ ጋር ወሰደው፥ ሐዋርያትም ከእርሱ ጋር ተቀበሉት፥ እንዲገረዝም አላገደዱትም፡፡
4. ለሐሰተኞች ወንድሞች ለአንድ ሰዓት እንኳ አልተገዙም፡፡
5. ከዚህም በላይ በስማቸው ዋና የነበሩት ምንም አልጨመሩብኝም ይላል፡፡
6. ሐዋርያት ለጳውሎስና በርናባስ የኅብረት ቀኝ እጆችን ሰጡ፡፡
ሠ. አምስተኛው እውነታ!
"ነገር ግን ኬፋ ወደ አንጾኪያ በመጣ ጊዜ ፊት ለፊት ተቃወምሁት፥ ይፈረድበት ዘንድ ይገባ ነበርና። አንዳንድ ከያዕቆብ ዘንድ ሳይመጡ ከአሕዛብ ጋር አብሮ ይበላ ነበርና፤ በመጡ ጊዜ ግን ከተገረዙት ወገን ያሉትን ፈርቶ ያፈገፍግ ነበርና ከእነርሱ ተለየ። የቀሩትም አይሁድ ደግሞ፥ በርናባስ ስንኳ በግብዝነታቸው እስከ ተሳበ ድረስ፥ ከእርሱ ጋር አብረው ግብዞች ሆኑ። ነገር ግን እንደ ወንጌል እውነት በቅንነት እንዳልሄዱ ባየሁ ጊዜ በሁሉ ፊት ኬፋን፦ አንተ አይሁዳዊ ሳለህ በአይሁድ ኑሮ ያይደለ በአሕዛብ ኑሮ ብትኖር፥ አሕዛብ በአይሁድ ኑሮ ሊኖሩ እንዴት ግድ አልሃቸው? አልሁት። እኛ በፍጥረት አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አሕዛብ አይደለንም፤" (ገላትያ 2፡11-15)
ጳውሎስ አዕማድ የነበረውን ጴጥሮስን ፊት ለፊት ተቃውሞ ወደ ወንጌል እውነት መልሶ ጠራው፡፡ ጴጥሮስን ከወንጌል እውነት ፈቀቅ ያለው ከያዕቆብ ዘንድ የመጡትን ሐሰተኛ ወንድሞች (ሳይላኩ የተላኩ አስመስለው የመጡትን) ፈርቶ ነበር፡፡
በገላትያ መጽሐፍ ከጌታ ከራሱ በጳውሎስ እጅ የተላከ እውነተኛው ወንጌል በፍጹም ንጽሕናው ተቀምጧል። በዚህ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ይህን ፍጹም ወንጌል የናፈቀው ሁሉ መላውን የገላትያ መጽሐፍ ማጥናት ይኖርበታል።
SUBSCRIBE
talewgualu video
https://www.youtube.com/watch?v=ANJk-wzRU_Q
Comments