ከጨለማ ወደ ብርሃን
ዮሐንስ 1፡4፥5
ነገሮች በህይወታችን በተሳሳተ መንገድ ሲሄዱ፥ ለዛውም እጅግ መጥፎ አቅጣጫ ሲጓዙ ብዙውን ጊዜ የሚሰጠው ምላሽ፥ የነገሩን መንስኤ ወደ ሌላው ሰው ማዞር አሊያም ሌሎችን መተቸት ነው። “ይሄ የእኔ ስህተት ሳይሆን የእንቶኔ ስህተት ነው” ይላል ደካማው ሰው። አልፎ ተርፎም እግዚአብሔር ላይ ጣት እስከ መቀሰር ይደርሳል፥ የራሱን ጽድቅ በራሱ መንገድ እንደሚሰራ ስለሚያምን።
እንዲህ ያለ ሰው የውስጡን በስቃይ የታጀበ አቤቱታ በሆዱ ይዞ የውሸት ሳቅ እየሳቀ መንገዱ አንደማያዋጣው ያውቃል፥ ግን የጀመረውን የጨለማ ጉዞ ሊገታው አይፈልግም። ይልቁኑ፥ የሌላውን ብርሃን ጉዞ ወቅሶና አንጓጦ ራሱን ነጻ ያወጣ ይመስለዋል፥ ራሱን በራሱ ሊያጽናና። ሆዱ እያወቀ፥ የሚሸነግላቸው፥ ለሰው የማይታዩ ግን በራሱ ግጣም የተሸፈኑ ብዙ ጉዳጉዶች በልቡ ጓዳ እንደሚርመሰመሱ ያውቃል። በአሻራ ምርመራ፥ እንኳን ሊገኙ የማይችሉ ተደርገው የተደበቁ ማንነቶች ሞልተውታልና።
አንድ ጊዜ፥ በአንድ ወዳጃችን ሱቅ ሌቦች ሰብረው ገብተው የተወሰነ ዕቃ ዘረፉ። ሲዘርፉ ያደረጉት ነገር ግን ፈጽሞ ለፖሊስ ምርመራ ከባድ የሆነ ነገር ነበር። ሌቦቹ ነካክተዋል ተብሎ የተገመቱት ቦታዎች በሙሉ ሲፈተሹ አንድም ለምርመራው ድጋፍ የሆኑ አስረጂ ምልክቶችን ትተው አላለፉም። ፖሊሶች እያንዳንዱን ስፍራ ሲፈትሹ አንድም ምልክት ማግኘት አልቻሉም። ምክንያቱም አሻራው እንዳይገኝ የሚያደርግ መሸፈኛ ሌቦቹ እጃቸው ላይ ተጠቅመው ነበረ። በተጨማሪም፥ የገነጠሉትን ቁልፎች እና ብረታብረቶች ሌቦቹ ውሃ ውስጥ ነክረው ሄደዋል። እናም ምርመራው ውጤት አልባ ሆነ። ግን ሌቦቹ ያላስተዋሉት ነገር በዛ ቤት ውስጥ ነበረ፥ የደህንነት ካሜራ በሱቁ ውስጥ ተገጥሞ እያንዳንዱን ድርጊት ይቀርጽ እንደነበር ጨርሶ አላወቁም።
የራሱ ጥፋት እንዳይገለጥ በራሱ ዘዴ አሻራውን ሰውሮ ሌላው ላይ ማላከክ ለምስኪኑ ሰው ለጊዜው ቀና መንገድ እና የሚያስመልጠው ይመስለዋል። የማይታየው ህሊናው ግን ፈጽሞ ጥፋቱን መሰወር ስለማይችል ነገሩ ንጹህ እንዳልሆነ በሂደት ያጋልጠዋል። ስለዚህ ድፍረቱ፥ ከአንዱ ስህተት ወደ ሌላ ስህተት፥ ከአንድ ጥፋት ወደ ሌላ ጥፋት ያሻግረዋል። የትናንት ድብቅነት ለነገው ስህተት ጉልበት እየሆነ ወደ ማይወጣው አዘቅት ሊከተው ተዘጋጅቷል።
. . . ቃሉ እንዲህ ይላል፤ “ብርሃን በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም አላሸነፈውም።”
የትኛው ጨለማ ነው ብርሃንን ማሸነፍ የሚችለው? የትኛው ድብቅ ማንነት ነው በብርሃን ፊት ከነ ኃያልነቱ መቆም የሚችለው? በእርግጥ ጉዳዩ ከሰው ሊሰወር ይችላል፥ ከኤክስሬይ፥ እና ከኤም አር አይ ወይም የትኛውም ቴክኖሎጂ ካመጣው የምርመራ ዘዴ ሊያመልጥ ይችላል። ከብርሃን ግን የትኛውም የጨለማ አቅም ሊያመልጥ ከቶ አይችልም።
. . . በክርስቶስ ህይወት ነበረች፥ ህይወትም የሰው ብርሃን ነበረች።
እይታ በኃጢዓት ሲሸፈን፥ በማንነት አዘቅት ውስጥ ተገብቶ በጨለማ ሲዳከር፥ በተከፈነ ማንነት፥ አሊያም በመንፈሳዊ ካባ የሰው ልጅ ሲመላለስ፤ በማዕረግ፥ በስም፥ በኃላፊነት፥ በሹመት እና በሽልማት መጋረጃዎች ያልሆነውን ሆኖ ሲገኝ፥ የገባበት የጨቀየ ህይወት በአንዳች ነገር ተከልሎ፥ ጨርሶ የማያውቀውን ህይወት ነኝ ብሎ ሲደሰኩር. . . ከህሊና ብርሃን ለማምለጥ እንደሞከረ ይኖራል. . . ራሱን እንዳታለለ። ግን እንዴት ሆኖ . . .!
መሬት እና ጥንቸል አንዴ ተጣሉ ይባላል። ጥንቸል መሬትን ባለ በሌለ ስድብ ሰድባት፥ ዞራ ላታያት ምላ ተገዝታ ሄደች፥ ሄደች፥ ሄደች. . . በነነች። ግን ሩጫዋን ገትታ ስትቆም ያለችው እዛው ነበረች።
ያልታረቀ ስብዕናን የተሸከመ ሰው፥ ከራሱ ጋር፥ ከአምላኩ ጋር እንደተጣላ የሚኖር ይመስለዋል። ግን ጥንቸሏን መስሎ ይኖራል እንጂ ከብርሃን ጋር ካልታረቀ ምን ሊረባው? ለነገሩ ይህ ሰው ምን ኃላፊነት ወይም አደራ ቢሰጠው ከሚያሳካው ይልቅ የሚያወድመው ይበዛበታል፤ መረጋጋትን የት አውቆት? እረፍትን የት አግኝቶት? እንደዋተተ የእውር ድንብር ይጓዛል፥ ይጓዛል፥በመጨረሻም ተገንዞ ይጋዛል! ደግሞ፥ ህመሙን እያወቀ ስለደበቀ፥ ማንነቱን ከድኖ አስመስሎ ስለኖረ በራስ መተማመኑን በገዛ እጁ ገደል ከቶታልና ፍርሃቱ፥ ብልጠቱ ሲያሰናክለው ይኖራል። የሚኖረው በጨለማ ነውና!
ለህዝብ ሁሉ የሚሆን ጨለማውን ሁሉ የሚገፍ ብርሃን ከዘመናት በፊት ለሰው ልጆች ሁሉ የምስራች ተብሏል። ይህ ህይወት የሆነ አስታራቂ ብርሃን፥ በጨለማ ይዳክር ለነበረ እና የሞት ስጋት ጣር ለሆነው ህዝብ ሁሉ የሆነ ብርሃን ነው። በኃጢዓትና በበደል ለተሸነፈ፥ ሰላሙን አጥቶ የሌላውን ሰላም ለሚነሳ፥ ሰው ሆኖ የወረደው አምላክ ብርሃን ሆኖ ወደዚህ በጨለማ ወደተዋጠው ዓለም መጥቷል። በእርሱ ዘንድ ጨለማ የለምና!
በጨለማ ሲሄድ የነበረው ህዝብ ከአላስካ እስከ ኒውዝላንድ ጫፍ ከሰሜን ዋልታ እስከ ኬፕ ጫፍ፥ ቋንቋ ሳይገድበው፥ ዘር እና ሃይማኖት ሳይወስኑት ወደዚህ ብርሃን እንደትናንቱ ዛሬም በመፍለስ ላይ ይገኛል። ብርሃን የበራለት ህዝብ፥ ሰላሙም በዛው ልክ ገደብ አልባ ሆኖለት የእርሱን በጎነት እንዲናገር ከድቅድቅ ጨለማ ወጥቶ፥ እስራቱ ተሰብሮ ጥሪውን ተቀብሎ ወደ መንግስቱ ፈልሷል።
የቀረኸው እና በጨለማ የምትዳክረው አንተ ነህ። ይኸውልህ ጥሪው ላንተ ነውና ወደዚህ ወደ ህይወት ብርሃን ና!
“በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ . . . ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው እሰራታቸውንም ሰበረ።” ተብሎ ተጽፏልና (መዝ. 107፡ 10 እና 14)
#Share
Comments