ወደ ደም እንዳልሄድ ህልናን የምሰጠው
ወደ ደም እንዳልሄድ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አዕምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ።
1ኛ ሳሙ. 25፡33
ይህን ንግግር የተናገረው የእስራኤል ንጉስ የነበረው ዳዊት ነው። አቢጊያ የተባለች ሴት ባልዋ ናባልን ዳዊት በምድረ በዳ ከንጉሱ ከሳዖል በሽሽት ላይ በነበረ ሰዓት በእጁ ከተገኘው የተወሰነ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጭፍሮቹን ልኮ ሲለምነው ለሰጠው አሉታዊ ምላሽ የናባል ሚስት
ላረገችው ተማጽኖ የሰጠው የምስጋና ቃል ነው። ክፍሉ ሰፊ ነውና እያንዳንዱ ሁኔታ ትንታኔ ቢሰጠው ብዙ ነገር ስለሚወጣው ያንን በመተው በተጠቀሰው ክፍል ላይ የተነሳውን ሀሳብ ብቻ ላሳይ።
ዳዊት በናባል ድርጊት ተበሳጭቷል። የተበሳጨበት አንዱ ምክንያት ከዚህ ቀደም ላደርግኩለት ደግነት ሁሉን እያወቀ በለመንኩት ሰዓት አመድ አፋሽ አድርጎኛል የሚል ነው። ልብ ሰባሪ ተማጽኖው “እረኞችህን ከቶ አልበደልናቸውም፥ በቀርሜሎስም በተቀመጡበት ዘመን ሁሉ ከመንጋው አንዳች አልጎደለባቸውም። ለዚህ ደግሞ በቂ ማስረጃ አለ፥ የመጀመሪያው የእንስሶችህ ጠባቂዎች የሆኑ እረኞችህ እና እኛ በሽፍትነት በነበርነበት ዘመን በየሜዳው ሲሰማሩ የነበሩ አንድም እንዳይነኩ አጥር ሆነን የጠበቅንልህ ንብረቶችህ ምስክሮች ናቸው”።
ጥያቄው ግልጽ ነው። ያኔ መልካም ነገርን ምንም ሳታደርግልን አድርገን ነበረ፤ ዛሬ ደግሞ አንተ በተራህ በጉድለታችን ሙላን፤ በችግራችን ደረስልን የሚል ትህትና የተሞላ ጥያቄ ነው ባለሀብቱ ጋ የሄደው። የናባል ምላሽ ግን ከስስትና ከስግብግብነት የመነጨ ክህደት ነበር። ይህ ክህደት የዳዊትን ብቻ ሳይሆን የአንባቢውን ጨጓራ እንደሚያበግን አልጠራጠርም። ደግ ላደረገ፥ ከለላ ለሆነ፥ ከምንም ተነስቶ ሀብትና ንብረትን ለጠበቀ ምላሹ ክፋት ሊሆን አይገባውም ነበረ፥ በአጭር ቃል!
ይሁንና ናባልን ትረፍ ሲለው በሚስቱ በኩል አስተዋይነት የተሞላው የተሰበቀ ጦርን፥ የተሰነዘረ ሰይፍን የሚመልስ መልካም ንግግር፥ ለራስና ለቤተሰብ ምህረትን ፍለጋ ያዘለች ነፍስ ጩኸት ንጉስ ዳዊት ጋ ሄደ። ደም እንዳይፈስ፥ ሰው እንዳይጠፋ፥ አካል እንዳይጎድልና ንብረት እንዳይወድም የሚያደርግ እርምጃ። ከማጋጋልና ከማባባስ ይልቅ ይቅርታን ሽታ ሰላምን የምትዘራ የምስኪን ድምጽ . . . ። ለሆዳም እና ቆንቋና ሰው ምሱ፥ ያለውን መንጠቅና ጉስቁልናን እስከ ጥግ እንዲያይ ማድረግ ነው። ቢሆንም ዳፋው ለራሷና ለቤቷ ነውና በገዳዩም ዘንድ በኃላ ላይ የህሊና ጸጸትና የሚነቀፍበት እንቅፋት እንዳይሆን፥ እግዚአብሔር የሰደዳት ትሁት ሴት ልመና ሆኖ ንጉስ ጋ ደረሰ።
የሴትየዋ ድርጊት ረቶት ከልቡ ይቅር ያለው ዳዊት፥ እንዲህ አላት “ወደ ደም እንዳልሄድ ፥ በእጄም በቀል እንዳላደርግ ዛሬ የከለከለኝ አዕምሮሽ የተመሰገነ ይሁን፥ አንቺም የተመሰገንሽ ሁኚ” ደም ከማፍሰስና ቤትን ከማፍረስ የመለሰኝ አዕምሮሽ የተመሰገነ ይሁን!
የአንዳንድ ሰው አዕምሮ፥ ንጉስን ወደ እርቅ፥ መንግስትን ወደ ምህረት፥ ህዝብን ወደ ሰላም መንገድ ይመራል። ውጥረትና ሽብር፥ ጠብና ጭቅጭቅ ከመስፋት ይልቅ የመመንመን ዕድላቸው በእነኝህ የሰላም ሰዎች ምክርና ተግሳጽ የሰፋ ነው። የሚያስተራርቁ ብጹዓን ናቸውና።
ዛሬ በሶሻል ሚዲያ የምንሰማው እና የምናየው ሀገርንና ህዝብን ወደ ደም እንዲሄድ የማድረግ አካሄድ ግን መቼ እንደሚቆም ግራ ይገባል። ትናንት ለተሰራ ጥፋት እንዲሁም ሳይሆነ ሆኗል በተባለ በፈጠራ ትርክት ደም እንዲፈስ፥ ሀገር እንዲተራመስ፥ ዳግም ንብረት እንዲወድም የሚደረገው አካሄድ የጤና ይሆን ያስብላል? የዛሬ ሠላሳ ዓመት ያህል የሩዋንዳን እልቂት እያነሳ እነሱን ሲተች የነበረ ጎጠኛ ጸሐፊ የሁቱዎችን ጥፋት ሊኮንን አንድም የሞራል ብቃት የለውም። ያለ ገደብ እዚህ በየፌስ ቡኩ ጥግ ስሙን እየቀየረ የሌላውን ዘር ሲሳደብና ሲቀስቅስ ይውል የለ። ወገኖች! ወደ ደም እንዳይኬድ ከመመለስ እና የበቀልን በትር ከማሳጠፍ ይልቅ ቤንዚን እያፈሰሱ የጥልን ምድጃ እያጋገሉ ማንደድ ትርፉ ምን ይሆን? ጎረቤትን ወደ ደም ማፍሰስ ማስኬድ፥ በየአደባባዩ ባልታረመ አንደበት የሀገርን ትርምስ መናፈቅና የሃይማኖትን ጠብ መጥራት ምን የሚሉትስ አባዜ ነው?
አዎን! እንደ አቢጊያ የተመሰገነ አዕምሮ ያላቸው፥ ጠብን አብራጅ የሆኑ ሴቶችና ወንዶች ኢትዮጵያዊያን ያስፈልጉናል። ሰላምን የሚዘሩ፥ እርቅን የሚያወርዱ፥ አንተም ተው አንቺም ተይ የሚሉ መልካም ሰዎች ያስፈልጉናል። ባለ አዕምሮዎችን ያብዛልን!
ነጋ
Comments