ወንጌል በምንም ነገር መቆም ስለማይችል ይቀጥላል
"ከዚያ ወዲያ ከአሥራ አራት ዓመት በኋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤ እንደተገለጠልኝም ወጣሁ፤ ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአሕዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኋቸው፤ ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኋቸው። ነገር ግን ከእኔ ጋር የነበረ ቲቶ እንኳ የግሪክ ሰው ሲሆን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፤" (ገላትያ 2:1-3)
ጳውሎስ ለ14 ዓመት ያህል ብቻውን የተገለጠለትን የፀጋውን ወንጌል ይሰብክ ነበር፡፡
ቲቶ ማነው? ጳውሎስ አይሁዳዊ ነው፣ በርናባስም አይሁዳዊ ነው፣ ቲቶ አህዛብ ነው፤ ምን ማለትነው? በአገልግሎትውስጥሊገቡወይምሊጠቀለሉከማይችሉሰዎች መካከል ነበር ማለት ነው፡፡
በአይሁዳዊ አስተሳሰብ ቲቶ አገልግሎት ውስጥ መግባት የለበትም፤ ሌሎች ሊጥሉት ወይም ሊቀበሉት የማይችሉትን ሰው እግዚአብሔር በራሱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አብቅቶ አገልጋይ ማድረግ እንደሚችል ቲቶ ምሣሌ ነው፡፡
የትኛውም ዓይነት ያለፈው ታሪካችን አያግደንም፤ እግዚአብሔር እንደ ቲቶ ብቁ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ምክንያቱም የመንፈስ አገልግሎት ራሳችንን ብቁ አድርገን የምንገባበት ሳይሆን እግዚአብሔር እኛን ብቁ ያደረገበት ነው፡፡
"እርሱም ደግሞ በመንፈስ እንጂ በፊደል ለማይሆን ለአዲስ ኪዳን አገልጋዮች እንሆን ዘንድ አበቃን፤ ፊደል ይገድላልና መንፈስ ግን ሕይወትን ይሰጣል።" (2 ቆሮንቶስ 3:6)
ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው እንደተገለጠለት ነው፤ ይህ ማለት እግዚአብሔር እንዲሄድ ነግሮታል (በምክንያት ነው የሄደው) ማለት ነው፡፡
የምናስተምረውን በተመለከተ በግል የምናናግራቸው ሰዎች ቢኖሩ መልካም ነው፡፡
በኢየሩሳሌም የነበሩ ስዎች መገረዝ የአህዛብ ስላልሆነ ቲቶን ይገረዝ ዘንድ ግድ አላሉትም፡፡
"ነገር ግን ባሪያዎች ሊያደርጉን በክርስቶስ ኢየሱስ ያለንን አርነታችንን ይሰልሉ ዘንድ ሾልከው በስውር ስለ ገቡ ስለ ሐሰተኞች ወንድሞች ነበረ። የወንጌልም እውነት በእናንተ ዘንድ ጸንቶ እንዲኖር ለአንድ ሰዓት እንኳ ለቅቀን አልተገዛንላቸውም።" (ገላትያ 2:4-5)
በገላቲያ የነበረው ችግር ራሳቸውን ልከው በመጡ (አዕማድ የሆኑት እውቅና ሰጠው ያላኳቸው) ሾልከው የገቡ ሐስተኛ ወንድሞች የፈጠሩት ሕግን ከመከተል ጋር የተያያዘ ችግር ነው፡፡
ነፃነታችንን ሊወስዱብን ወይም ሊገፉን የሚችሉ አስተሳሰቦችን መቀበል የለብንም፤ ጳውሎስ ለእነዚህ ሐሰተኛ ወንድሞች ለአንድ ሰዓት እንኳ ተሸንፈን አልተገዛንላቸውም ይላል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ለተገለጠልን እውነት ሊኖረን የሚገባውን መሰጠት ነው፡፡
የሕግ አስተሳሰብ ለመባረክ፣ ለመቀባት፣ ይህንንና ያንን ለማግኘት መጀመሪያ አንተ ከዚያ እግዚአብሔር የሚል ነው፤ እንደ አዲስ ኪዳን አማኝ መረዳት ያለብን አደገኛው አጋንንት ሳይሆን በክርስቶስ የተፈፀመውን ሥራ ከንቱ የሚያደርግ የሕግ አስተምህሮ መሆኑን ነው፡፡
ለወንጌል እውነት የሚደረግ ትግል ይቀጥላል፤ ስለዚህም በአመለካከታቸው ስለሚያፈገፍጉት ግራ መጋባት የለብንም በክርስቶስ ያለው ሕይወት ሥርዓት አልባ እንዲሆኑ ካደረገ በሌላ አባባል ክርስቶስ ሥርዓት አልባ ነበር ማለታቸው ነው፡፡
መጀመሪያ ወደ ገላቲያ የገባው ወንጌል፤ ጳውሎስ የፈለገው ሌላ ነገር ተጨማሪ እንዳይሆን ይህ ወንጌል እንዲቀጥል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እያለ ያለው ወንጌል ቆሞ ሕግ እንዲገዛ አንፈልግም ነው፡፡
ጳውሎስ የወንጌሉን ተአማኒነትና ምንጭ ብቻ ሳይሆን አዕማድ (ዋነኞች) የሆኑት በተገለጠለት ወንጌል ላይ ምንም እንዳልጨመሩለት ይናገራል፡፡
"አለቆች የመሰሉት ግን፥ በፊት ማን እንደ ነበሩ አይገደኝም፤ እግዚአብሔር የሰውን ፊት አይቶ አያደላም፤ አለቆች የመሰሉት አንዳች እንኳ አልጨመሩልኝምና፥ ተመልሰው ግን ጴጥሮስ ለተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠው እንዲሁ ለእኔ ላልተገረዙት የሆነው ወንጌል አደራ እንደ ተሰጠኝ አዩ፤ ለተገረዙት ሐዋርያ እንዲሆን ለጴጥሮስ የሠራለት፥ ለእኔ ደግሞ ለአሕዛብ ሐዋርያ እንድሆን ሠርቶአልና። ደግሞ የተሰጠኝን ጸጋ አውቀው፥ አዕማድ መስለው የሚታዩ ያዕቆብና ኬፋ ዮሐንስም እኛ ወደ አሕዛብ እነርሱም ወደ ተገረዙት ይሄዱ ዘንድ ለእኔና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጡን፤ ድሆችን እናስብ ዘንድ ብቻ ለመኑን፥ ይህንም ደግሞ ላደርግ ተጋሁ።" ገላትያ 2:6-10
ጳውሎስ ልክ ጴጥሮስ ለተገረዙት አይሁድ ሐዋሪያ ሊሆን እንደተጠራ እርሱም ላልተገረዙት አሕዛብ ሐዋሪያ እንዲሆን የተጠራ ነው፤ እርሱ ለአሕዛብ ወንጌልን ለመስበክ የተወሰነ ጥሪ የተሰጠው ነው፡፡ ኤፌሶን 3:6
ጳውሎስ ራሱን ሲጠራ "ጳውሎስ ሐዋሪያ" እንጂ "ሐዋሪያው ጳውሎስ" በማለት አይደለም፤ ይህ ማለት እርሱ የሚቆጥረው እንደ ተግባር እንጂ እንደ መጠሪያ አይደለምና፡፡
"ነገር ግን ሩጫዬንና ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን አገልግሎት እርሱም የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር እፈጽም ዘንድ ነፍሴን በእኔ ዘንድ እንደማትከብር እንደ ከንቱ ነገር እቆጥራለሁ።" የሐዋርያት ሥራ 20፡24
"ስለዚህም አሕዛብ ስለ ሆናችሁ ስለ እናንተ የክርስቶስ ኢየሱስ እስር የሆንሁ እኔ ጳውሎስ ለእግዚአብሔር እንበረከካለሁ። ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤ ይህንም ስታነቡ የክርስቶስን ምሥጢር እንዴት እንደማስተውል ልትመለከቱ ትችላላችሁ፤ ይህም፥ አሕዛብ አብረው እንዲወርሱ፥ በአንድ አካልም አብረው እንዲሆኑ፥ በወንጌልም መስበክ በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነ የተስፋ ቃል አብረው እንዲካፈሉ፥ ለቅዱሳን ሐዋርያትና ለነቢያት በመንፈስ አሁን እንደ ተገለጠ በሌሎቹ ትውልዶች ዘንድ ለሰው ልጆች አልታወቀም። እንደ ኃይሉ ሥራ እንደ ተሰጠኝም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ስጦታ መጠንየወንጌል አገልጋይ ሆንሁለት።" ኤፌሶን 3፡1-7
"ስለ እናንተ እንደ ተሰጠኝ እንደ እግዚአብሔር መጋቢነት፥ የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽሜ እንድሰብክ እኔ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ሆንሁ።" ቆላስይስ 1፡25
አዲስ ኪዳንን ስናጠና ሐዋሪያው ጳውሎስ የፀጋውን (እውነተኛውን) ወንጌል ለመስበክ የተመረጠ እና ከሌሎች ይልቅ የአዲስ ኪዳንን መገለጥ የተቀበለ መሆኑን እንረዳለን፡፡
Comments