የተረሳው ትንቢታዊ መልእክት

 የተረሳው ትንቢታዊ መልእክት 


አሁን የእኔ የሚባልበት ዘመን አብቅቷል የክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንደ አካል የምትገለጥበት ዘመን ነው። እግዚአብሔር የሰጠው የአካል ሕይወትን ነው። ስልጣንም የሚሠራው በአካል ውስጥ ነው። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ 12 ቁጥር 27 ላይ "እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ" ይላል። ይህንን በሚገባ የተረዳነው አይመስለኝም። የተባልነው "እናንተ" እንጂ "አንተ ወይም አንተ" የክርስቶስ ብልት ነህ እንጂ አካል ልትሆን አትችልም። በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልም። ቢሞከር እንኳ የሚሰማ ድምፅ አይኖርም። የማንነታችን መገለጫው የክርስቶስ አካልነታችን ነው። 


የሚያስፈልገን ርችት ሳይሆን ብርሃን ነው። አካልነት የዝና ሳይሆን ሕይወትን የመኖር ጉዳይ ነው። የአካል ሕይወትን የመኖር ጉዳይ ትንሣኤን ማግኘት አለበት። የክረምት ውሃ እንደሚያልፍ የግለኝነት ዘመን እንዲሁ አልፏል። የሕይወት ጉዳይ ተረት አይደለም። 


እንዴት ወደ አካል ሕይወት ውስጥ እንመለሳለን ነው ቀጣዩ ጥያቄ። ለሁሉ ዘመን ነበረውና የግለኝነት ዘመን አሁን አብቅቷል። የግለሰብ ጉዳይ ውስን ነው፣ ዓይን ከሆንክ ማየት ብቻ ነው የምትችለው። አሞራ መጥታ አንስታህ ትሄዳለች። እግር የለህምና አትሮጥማ፣ እጅ የለህምና ራስህን አትከላከልማ። 


ፎቶው በሴሚናሩ የተናገረውን አንድ ከባድ ንግግሩን እንዳስታውስ አደረገኝ። "ወይ ወንጌል ይዘህ ገጠር ትገባለህ ወይ ከተማ ትበሰብሳለህ"


ዛሬ ዶክመንት በምፈልግበት ጊዜ የዛሬ 10 ዓመት በ2002 ዓ.ም የታተመ ኤፍታህ ቅጽ 2 ቁጥር 1 መጽሔት አገኘው። ጽሑፉ ለትውስታ ያህል ብቻ ቆንጥሬ የወሰድኩት ሲሆን ጥቅምት 15/2002 ዓ.ም በእርሱ ባለራዕይነት በተተከለችው ሬማ አገልግሎት አዲስ አበባ ቤተክርስቲያን በተዘጋጀው የመሪዎች እና የአገልጋዮች ሴሚናር ላይ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያው ዜድ በኩል የተናገረው ነው። 


መጽሔቱን ሳነበው አንድ ነገር አስተዋልኩ መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያው ዜድ በኩል ያስተላለፈው መልእክት ትንቢታዊ መልእክት ነበር። ይሁን እንጂ በሴሚናሩ ቦታ የነበርን ሰዎች መልእክቱን እዚያው የጣልነው መጽሔቱን ደግሞ ያነበቡ ሰዎች እዚያው መጽሔቱ ላይ በንባብ የተውት መሆኑን አረጋገጥኩኝ።


"መንፈሳዊ ሕብረት በልዩነት አንድነትን ለመመስረት ካልሆነ በቀር በእግዚአብሔር ቃል እውነት በመመስረት እንጂ በሰዋዊ መዋቅር እና በመደራጀት አይመጣም" (ከእኔ)


በመጨረሻም ይህችን መልእክት ለመጋቢ አመሉጌታ አድርሱልኝ። የአባቶችን ታሪክ መፃፍ በጀመሩ ብዕሮችህ የዚህን ወንጌል በተግባር የሆነውን የሐዋርያው ዜድን ታሪክ ከትበው በሉልኝ።

Comments