የክርስቶስ ፍቅር

 የክርስቶስ ፍቅር

አንዳንድ ሰዎች ብዙ ጊዜ ጌታን እናገለግላለን እያሉ ሲናገሩ እንሰማለን። ይሁን እንጂ ብዙ ነገር ሲያበላሹ ደግሞ ይታያል። አንዳንዶች ጥቃትን በጥቃት ይመልሳሉ፤ ለሚናገራቸው ሁሉ ወዲያው አጸፋውን ይመልሳሉ። ከዚህ በተቃራኒው ጥቃትን በትዕግስት የሚያሳልፉት አማኞች ወይንም ክፉ ሲናገሩት ጌታ ይባርክህ ብሎ የሚያሳልፉ አማኝ ሲያዩ እንደሞኝ ወይንም እንደ ኋላ ቀር ይቆጥሩታል።


በዘመናችን ለራስ ጥቅም የማይሮጥ ሰው በማህበረሰቡ ዘንድ ያልተለመደ እንግዳ ነው። ዓለም ቁጥር አንድ ራስን ማስቀደም የሚል ፍልስፍና አላት ወይንም ምቹ ጊዜ እስኪገኝ ድረስ ራስን መደበቅ ሌላው ፍልስፍና ነው። በመስቀሉ የተቃኘ ሕይወት ያለው እውነተኛ ክርስቲያን ግን ሁልጊዜ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ስለሚለው የሚያስቀድመው የሌላውን ጥቅም ነው የራሱን ሁሉ እያጣ። ምክንያቱም አንድን እውነተኛ አማኝ የሚያንቀሳቅሰው የክርስቶስ ፍቅር መሆኑን ልብ ልንለው ይገባል፤ ቃሉ እንዲህ ይላልና፦ 


"ይህን የምለው ራሳችንን በእናንተ ፊት እንደ ገና ለማመስገን ሳይሆን፣ በእኛ እንድትመኩ ዕድል ልሰጣችሁ ነው፤ ይኸውም በውጭ በሚታየው ለሚመኩት እንጂ በልብ ውስጥ ባለው ነገር ለማይመኩ መልስ መስጠት እንድትችሉ ነው። ከአእምሮ ውጪ ብንሆን ለእግዚአብሔር ብለን ነው፤ ባለ አእምሮም ብንሆን ለእናንተ ነው። 


የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናልና፤ ምክንያቱም አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች ሆነናል፣ ከዚህም የተነሣ ሁሉ ሞተዋል። በሕይወት ያሉትም ለሞተላቸውና ከሙታን ለተነሣላቸው እንጂ ከእንግዲህ ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ።"( 2ቆሮ 5፥12-15 )

Comments