የመንፈስ ቅዱስ ሥራ!


"እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።" (ኤፌሶን 1፡13-14)


"እናንተም ደግሞ የእውነትን ቃል፥ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፥ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፥" ከዚህ ቃል የምንረዳው አንድ ሰው ለመዳን የመዳኑን ወንጌል መስማት እና በክርስቶስ ማመን እንዳለበት ነው፡፡ 


ድኅነት ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን እግዚአብሔር ለእኛ አስቀድሞ የወሰነው ታላቅ እቅድ ነው፡፡ ይህም ድኅነት እጅግ አስደናቂ እና የከበረ ነው፡፡ 


ድኅነት በህይወታችን ተግባራዊ የሚሆነው በሰማነው ወንጌል ላይ ባለን እውነተኛ እምነት ነው፡፡ ይህ እውነተኛ እምነት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውጪ በአዲስ ኪዳን የለም፡፡ 


መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን እንድንረዳና ይህ በክርስቶስ የተከናወነው ሁሉ ለእኔ ነው ማለት እንድንችል ብርሃንን ይሰጠናል፡፡ 


ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ በሚመጣበት ጊዜ በሦስት አቅጣጫዎች ሰዎችን በመውቀስ  እንደሚሠራ ተናገረ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ሰው ኩነኔ ቢሰማው ከእርሱ እንዳይደለ ማወቅ አለበት፡፡ 


"እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤ እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።" (ዮሐንስ 16:7)


መንፈስ ቅዱስ ይህንን ሥራውን አድርጎታል? አዎ አድርጎታል! አሁንም እያደረገው ነው።


ሰዎች ለሰሙት ወንጌል ምላሽ መስጠት የሚችሉት ተገደው ሳይሆን መንፈስ ቅዱስ በልባቸው ላይ በሚሠራው ሥራ ብቻ ነው፡፡


ከመንፈስ ቅዱስ ውጪ የእግዚአብሔር መነካት እና ለድኅነት የሆነ የአዲስ ኪዳን እምነት/ የክርስቶስ እምነት የለም፡፡


ሀ. ልብን መንካት፡- በበዓለ ሃምሣ ቀን በጴጥሮስ ስብከት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፡፡ 


"ይህንም በሰሙ ጊዜ ልባቸው ተነካ፥ ጴጥሮስንና ሌሎችንም ሐዋርያት፦ ወንድሞች ሆይ፥ ምን እናድርግ? አሉአቸው። ጴጥሮስም፦ ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።" (ሐዋርያት ሥራ 2:37-38)


ለ. ልብን መክፈት፡- በጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ነው፡፡ 


"ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።" (ሐዋርያት ሥራ 16:14)

"በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤ እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።" (ኤፌሶን 1፡14)


"በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ፤"  ይህ ቃል የሚያሳየን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ማኅተም መሆኑን ነው፡፡ ማኅተም ራሱ መንፈስ ቅዱስ ነው፣ እናም አማኙ ውስጥ መገኘቱ ባለቤትነትን እና ደህንነትን ያመለክታል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ መታተም ስሜት ወይም አንዳንድ ምስጢራዊ ውስጣዊ ተመክሮዎች አይደለም፡፡ 


ታተማችሁ (ሰፍራጊዞ - sphragizo):- ባለቤትነትን፣ ባለንበረትነትን የሚያመለክት የተቀረጸ ዓርማ፣ ጽሁፍ ወይም ማሕተም ማድረግ፤ ወይ አንድን ሰነድ፣ ጽሁፍ፣ ደብዳቤ ወይም ማንኛውንም አይነት ንብረት በቀለጠ ሰም ማሸግ፡፡ ማሕተሞች አገልግሎታቸው የታተመበት ነገር ትክክለኛ መሆኑን፣ ይዘቱ ሳይለወጥ ሳይበረዝ መጀመሪያ እንደነበር ተጠብቆ መቆየቱን ማረጋገጥ ነው፡፡  


ሐዋርያ ሊሆን የተጠራው ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ መልዕክቱ በምዕራፍ 6 ከቁጥር 19 እስከ 20 ባለው ክፍል እኛ የእግዚአብሔር እንደሆንን ይናገራል፡፡ 


ጳውሎስ በሮሜ ምዕራፍ 8 ቁጥር 23 ላይ በፍጻሜ ቀን የሚደረግልን ቤዛነት እርግጥ መሆኑን በአፅንኦት ገልጿል፡፡


እኛ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች ለመሆናችን ውስጣዊ ምስክርነትን የሚሰጠን መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ 


"የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል።" (ሮሜ 8:16)


"እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥" ርስት የሚለው ቃል ውርስን ለማመልከት ሲሆን መያዣ የሚለው ደግሞ ሊቆጠርና ሊሰፈር ከማይችለው ከሚጠብቀን ርስት ላይ እንደ ቅምሻ ማግኘትን ለማመልከት ነው፡፡


መያዣ/ቀብድ (አራቦን - arrabon)፡- በእንግሊዘኛው (earnest - money ወይም deopist) የሚለው ሲሆን በጥንቱ የግሪኮች ንግድ ሥርዓት ውስጥ በጣም የታወቀ ቃል ነበር፡፡ አንድ እቃ ሲገዛ አስቀድሞ የሚሰጥ ከፊል ክፍያ ነበረ፤ ይህም ቀሪው ሙሉ ክፍያ በጊዜው እንደሚከፈል ዋስትና መስጫ ነበረ፡፡ እስከዛሬ ድረስ ብዙ የጥንት ግሪክ የንግድ ሰነዶች ውስጥ ቃሉ ይገኛል፡፡ 


እግዚአብሔር የዘላለም ርስት እንዳዘጋጀልን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።


"ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።" (ሮሜ 8:17)


"ይህም ርስት በመጨረሻው ዘመን ይገለጥ ዘንድ ለተዘጋጀ መዳን በእምነት በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል።" (1 ጴጥሮስ 1:5) 


"ለእግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ፥ ይህም ለክብሩ ምስጋና ይሆናል።" በትንሳኤ እና በክብር በእግዚአብሔር "ሙሉ በሙሉ" እስክንገዛ ድረስ ይህ ዋስትና አለን፡፡ 


መዋጀት (አፖሉተሮሲስ - apolytrosis):- በአዲስ ኪዳን የቤዛ ክፍያ በመክፈል ሰውን ከኃጢአት ኃይል ነጻ እና ከአዳም ከተወረሰው አሮጌ ባህርይ ነጻ ስለመውጣት የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ 


ርስት ምንም እንኳን የተሰጠንና የተዘጋጀልን ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የምንወርሰው ግን ወደፊት ነው። ስለዚህ ርስት የቅዱሳን ተስፋ ነው። እግዚአብሔር ለድኅነት ብቻ አልጠራንምና ነገር ግን ለርስትና ለታላቅም ተስፋ እንጂ።


መዳን ሦስት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነርሱም መጽደቅ (Righteousness)፣ መቀደስ (Sanctification) እና መክበር (Glorification) ናቸው፡፡ በጴጥሮስ መልዕክት ድነት የተባለው እግዚአብሔር ሟች የሆነውን የአማኙን ሥጋ የማይሞት አካል አድርጎ መለወጡን (መክበር - Glorification) ያመለክታል፡፡

Comments