ተስፋ መቁረጥ
ተስፋ የቆረጠ ሰው ነገን ሳይሆን ዛሬን ብቻ ያስባል፤ ለዚህም በኃጢአት ላይ ኃጢአት በበደል ላይ በደል ሲሰራ ይኖራል፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ግዴለሽና ራሱን የሚጥል ይሆናል፡፡ ቀናት የሚተካኩ እርሱን ለመጉዳት ይመስለዋል፡፡ አንተ ግን ከዚህ ተስፋ መቁረጥ ስሜት መውጣት ያስፈልግሃል፡፡ በምንም ዓይነት ፈተና ውስጥ ብትወድቅ ኢዮብን ሁልጊዜ እያስታወስክ ተስፋህን ማለምለም አለብህ።
ተስፋህን የሚያጨልምብህ ጠላት ብቻ ነው፤ እርሱ ደግሞ በዚህ ምድር ያለህን ቆይታ እስክትፈጽም ድረስ ተስፋህን አጨልሞ ለዘለዓለም ለራሱ ብቻ አድርጎ መኖር የሚሻ የማይራራ ክፉ ጠላት ነው፡፡ ስለዚህ ተስፋ የምታደርገው ነገር መኖር አለበት፡፡ ለነገ ተስፋ የሌለው ሰው የዛሬን መምሸት አብዝቶ ይቃወማል፡፡
ስለዚህ አንተ ከዚህ የተስፋ ቢስነትና የተስፋ ቆራጭነት ስሜት መውጣት ያስፈልግሃል፡፡ ራስህንም በቀናው መንፈስ ማደስ ያስፈልግሃል፡፡ አንተ ተስፋ የምታደርጋት ርስት መንግሥተ ሰማያትን ነው፡፡ ለአንተ ከዚህ የበለጠ ተስፋ ካለህ ፥ በቃ ተስፋ እንደሌለህ፤ ተስፋ እንደቆረጥህ በዚህ ተረዳ፡፡ ተስፋህ ሃብት ንብረት ማፍራት፣ ቤት መሥራት፣ ቤተሰብ መመሥረት ብቻ ከሆነ እነዚህ ሲሟሉልህ አምላክህን መርሳትህ አይቀሬ ነውና፡፡
ስለዚህ ተስፋ የመቁረጥ ስሜትህን ማራቅ አለብህ፡፡ ምክንያቱም ሰው በስሜት ሲመራ ያው ስሜት እንደ ሚነጥር ኳስ ነውና መጨረሻው ማረፊያው አይቃወቅም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመስርተን መረባችንን ( ህይወታችንን ) ስንጥል ፍሬያማ ወይም ባለ ሙሉ ተስፋ ተካፋይ እንሆናለን። እንዲሁም ተስፋህ ሊሆን የሚገባው ሁኔታዎች ፣ ሰዎች ላይ ሳይሆን የክብር ተስፋ ያለው ክርስቶስ እየሱስ ላይ ብቻ መሆን አለበት። እንግዲህ ውድ ወዳጆቼ ለዛሬ የነበረኝ መልዕክተ የእስከ አሁኑን ይመስል ነበር፤ ሁላችሁንም በጣም እወዳችኋለሁ በነገር ሁሉ ተባረኩ፡፡
Comments