ወደ መስቀሉ እንመልከት

 "ወደ መስቀሉ እንመልከት"


የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ድንቅ የወጣቶች ፕሮግራም! 


1ቆሮንቶስ 1:18-31


የፋሲካ (የትንሳኤ) በዓል በህይወታችን ልዩ ትርጉም አለው። እግዚአብሔር የሰራቸው ብዙ አስገራሚ እና አስደናቂ ነገሮች አሉ። በቀራንዮ መስቀል ላይ የተሰራው ግን ከሁሉም ልዩ እና አስደናቂ ስራ ነው። እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር የገለጠበት ቦታ ቢኖር በመስቀል ላይ ነው። 


ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ አላቸው፣ "በመካከላችሁ ሳለሁ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ ቆርጬ ነበርና" 1ቆሮ 2:2. ይህም ማለት የወንጌላችን ማዕከል የሆነውን መልእክት "እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" 1ቆሮ 1:23 ያሳየናል። 


ቆሮንቶስ የግሪክ ከተማ ስትሆን በጠቢባ እና በምድራዊ እውቀት የተካኑ ሰዎች የሚኖባት ከተማ ነበረች። ከዚህም የተነሳ ለቆሮንቶሳውያን ስለ መስቀሉ መናገር #ሞኝነት ነበር። ዋጋ የሌለው ተራ ነገር ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር እንዲህ አለ።  ጠቢባን ነን የሚሉትን እንዲህ ብሎ ይጠይቃቸዋል። ጥበበኛ የት አለ? ጸሐፊስ የት አለ? የዚህ አለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረግምን? ብሎ ይጥይቃል። ምክንያቱም ዓለም በጠቢባን፣ በጸሐፊዎችና በመርማሪዎች የተሞላች ቢመስላትም ውስብስብ የሆነውን የሰው ልጅ ጥያቄን መመለስ አልቻለችምና ነው። 


የሰው ልጅ በሀጥአት ወድቆ ካመጣው ችግርና ጣጣ ሊያድን የሚችለው ለብዙዎች ሞኝነት የተባለው የቀራንዮ መስቀል ላይ ሥራ ነው። 


ዛሬ የመስቀሉ ቃል በብዙዎች ዘንድ ቀልሎ የታያል። ዓለምም ምልክቶቻችንን በማጥፋት ቀስ እያለች ክርስቶስን ከልባችን ለማውጣት እየተጋች ትገኛለች። ለዚያ ነው ዛሬ የምንታወቅበት ልዩ ምልክታችን በመጥፋት ምልክት አልባ፣ ርዕስ አልባና  ለሙጥ ሃይማኖት እያስፋፋን ያለነው። ክርስቶስ ለእኛ የሆነልንን ቦታ ማንም ልሸፍን አይችልም። ዛሬም እግዚአብሔር ወደ መስቀሉ እንድንመለከት ይፈልጋል። ለምን? 


ወደ መስቀሉ ስንመለከት የዓለም ሀጥአተኝነት፣ ሀጥአት በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ መሆኑን፣ የእግዚአብሔር ፍቅርና ቸርነት እና ድል ነሺነትን እንመልከታለን። 


ጌታ ኢየሱስ ምንም ሳያጠፋ በወንበዴ ሞት እንዲሞት ዓለም ፈርዳበታለች። ኢየሱስን የወጋው እጅ አልተቆረጠም ዛሬም አለ። የተሳደበውም አንደበት እስካሁንም ከእኛው ጋር አለ። ይህ የሚያሳየው የሰው ተፈጥሮ እንደማይቀየር ነው። ዛሬም የሰው ልጅ ሀጥአተኛ ስለሆነ ወደ መስቀሉ መመልከት ያስፈልጋል። 


እግዚአብሔር ለሀጥአተኛ የሚራራ ቢሆንም ለሀጥአት ግን አይራራም። ሀጥአት የምትሰራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች እንዳለው የሀጥአት ደመወዝ ሞት ነው። የእኔ እና የእናንተን ሀጥአት ተሸክሞ የተገኘው ኢየሱስ ራሱ በሞት ተቀጥቷል። እግዚአብሔር ከሀጥአት ጋር ጨዋታ አያውቅም። ነገር ግን በመስቀሉ ላይ በተሰራው ስራ የሀጥአት ስርየት አግንተናል። ዛሬም ወደ መስቀሉ ስንመለከት እግዚአብሔር ሀጥአትን በጣም እንደሚጠላ ተረድተን ወደ ንስሃ እንመጣለን። 


መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፣ "ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም" ዮሐ 15:13። በመስቀሉ ላይ ከተገለጠልን ፍቅር በላይ እግዚአብሔር ሌላ ፍቅርን ለእኛ የሚገልጥበት መንገድ የለውም። ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውምና። ስለዚህ ወደ መስቀሉ ስንመለከት የእግዚአብሔርን ፍቅርና ቸርነት እንመለከታለን። 


በመጨረሻም ሞት ድል የተደረገው በመስቀሉ ስራ ነው። ሰሞኑን በምናከብረው በትንሳኤ ኃይል ነው የሞት እና የሀጥአት ገልበት የተመታው። ድል አድራጊ በሆነው በክርስቶስ የተነሳ እኛም ዛሬ ወደ መስቀሉ ስንመለከት ከዓለም፣ ለሀጥአትና ከስጋ በላይ ሆነን በድል እንመላለሳለን። "የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ"  ገላ 5:24 እል የለ መጽሐፉ? 

የቃል ጊዜ:- በአገልጋይ አለማየሁ ሆጤሣ

ዝማሬ:- በቤተ ክርስቲያኒቱ ዝማሬ ቡድን 

የተለያዩ አገልግሎቶች:- ግጥም እና የእለቱ የቤተ ክርስቲያኒቱ ፕሮግራሞች በሙሉ በወጣቶች ተሸፍኗል። 

እሁድ ሚያዝያ 17/2013 ዓ. ም

Comments