አድዋና ጎልጎታ-- የሁለት ድሎች ወግ
አንዱ አድዋ ተራራ ላይ። ሌላው ጎልጎታ ኮረብታ ላይ። አንዱ በመግደል የተገኘ ድል። ሌላው ለሌሎች በመሞት የተገኘ ድል። አንዱ ምድራዊ ድል። ሌላው ሰማያዊ ድል። አንዱ ታሪካዊና ብሔራዊ ድል። ሌላው ዘላለማዊና አጽናፈ ዓለማዊ ድል። አንዱ ለምድራዊና ለጊዜያዊ ነጻነት ሌላው ለሰማያዊና ለዘላለማዊ ነጻነት። አንዱ ሥጋዊ ድል ሌላው መንፈሳዊ ድል። አንዱ ሐጢአት የተገለጠበት ድል ሌላው ሐጢአት የተወገደበት ድል።...
አለም ብዙ ጦርነቶችን ተዋግቷል። ሁሉም ጦርነቶች አሸናፊዎችና ተሸናፊዎች አሉዋቸው። የሁሉም ጦርነቶች መርህ ሌላውን መግደል እንጂ ለሌላው መሞት አይደለም። በአለም ቋንቋ ድል ማለት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች መግደልና መማረክ ነው። ይህ መርህ ስጋዊ መርህ ነው። የዚህ መርህ አርቃቂ ሌላ ሳይሆን ራሱ ሰይጣን ነው። ሐጢአትን ሳይሆን ሐጢአተኛውን መግደል። መርዙን ማጥፋት ትቶ መርዘኛውን ማጥፋት። አለም ይህንን መርህ ሲከተል ከአዙሪቱ ውስጥ እስከ ዛሬ አልወጣም።
የመለኮት መርህ የዚህ ተቃራኒ ነው። መግደል ሳይሆን ማዳን ነው። ሌላውን ማጥፋት ሳይሆን ለሌላው መሞት ነው። ይህ የመለኮት መርህ በተጨባጭ የተገለጠው በኢየሱስ ነው። ኢየሱስ በዚህ ምድር ላይ የተወለደው ለመግደል ሳይሆን ለመሞት፣ ለማጥፋት ሳይሆን ለማዳን ነበር። (ማቴዎስ 1:21) ኢየሱስ የመለኮትን መርህ ተግባራዊ ለማድረግ የሰውን ዘር ከነሐጢአቱ በራሱ ላይ በመሸከም ከጽድቅ ለራቀው ሕዝብ ጽድቅን ለመስጠት ተጠመቀና "ጽድቅን ሁሉ ፈጸመ።" (ማቴዎስ 3:15፤ ሮሜ 6:3-5)
በሐጢአት የተመረዘውን ሐጢአተኛ ሰው ለማዳን ሐጢአት የተባለውን መርዝ በራሱ ለማስወገድ (1ኛ ዮሐንስ 3:5) "የአለምን ሐጢአት የሚያስወግድ በግ" (ዮሐንስ 1:29) ሆነ። በጎልጎታ ኮረብታ በመስቀል ላይ ለሰው ዘር ሐጢአት ደሙን አፍስሶ በመሞትም (1ኛ ቆሮንቶስ 15:3) ኢየሱስ የሐጢአትን ችግር በጥምቀቱ በሞቱና በትንሳኤው ከፈታ በኋላ "አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ #ድል #በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።" (ቆላስይስ 2:15) እርሱ "ሐጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በግርማው ቀኝ ተቀመጠ።" (ዕብራውያን 1:3)
እውነተኛው ድል የሐጢአት ጀማሪውና ሐጢአት ራሱ የተሸነፈበት ድል ነው። እውነተኛው ድል የሰው ዘር ከሐጢአት ባርነት ነጻ የወጣበት በኢየሱስ ጥምቀት፣ ሞትና ትንሳኤ የተገኘው ነጻነት ነው። የአድዋና የጎልጎታ ልዩነት ይህ ነው።
Comments